በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ዋልታ የሆኑት ኢትዮጵያ እና ኬንያ ያላቸው የቀደመ ታሪካዊ ትስስር እና ወዳጅነት ከጠንካራ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ባሻገር የቀጣናውን የልማትና የዲጂታል ምህዳር ወደሚቀይር ስትራቴጂያዊ ቁርኝት ተሸጋግሯል።
ሁለቱ ሀገራት የጀግንነት እና የሉዓላዊነት የጋራ ታሪክ ያላቸው ሲሆን፣ ይኸው የቆየ መሠረት ዛሬ ላይ የሕዝቦቻቸውን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጋራ ለመቅረጽ የሚያስችል ጽኑ መደላድል ፈጥሯል።
ይህ ቀደምት ወዳጅነት በአሁኑ ወቅት በዘመናዊ የልማት ዘርፎች ላይ ተመስርቶ እጅ ለእጅ ተያይዞ የመጓዝ አዲስ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ የኬንያው ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ገብቶ በስፋት መንቀሳቀሱ የሁለቱ ሀገራት የቴክኖሎጂ፣ የዲጂታል ፋይናንስ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለመሸጋገሩ ማሳያ ነው።
ሁለቱ ሀገራት ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም እና ደህንነት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የጎላ ከመሆኑም በላይ፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን በተግባር በመምራት ረገድ ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ላይ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኤልዶሬት በተከበረው የ"ማሹጃ" የጀግኖች ቀን ብሔራዊ በዓል ላይ በመገኘት በኬንያ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የቆየ ወዳጅነት ይበልጥ ያጠናከረ ሆኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በክብረ በዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በታሪካዊ ዳራቸው የተሳሰሩ የሆኑት የሁለቱ ሀገራት የወደፊት ዕጣ ፈንታም በጋራ ልማትና ብልጽግና የተሳሰረ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኬንያ ጉብኝት ሁለቱ ሀገራት በጋራ ታሪክ፣ በሕዝብ ለሕዝብ፣ በንጹህ ኃይል፣ በመሠረተ ልማት እና በንግድ ያላቸውን የቆየ ትስስር ወደ አዲስ የስትራቴጂያዊ አጋርነት የከፍታ ምዕራፍ ላይ ያሸጋገረ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ውህደት ትልቅ ማሳያ ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: