ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት ሞስኮ በሚካሄደው ሦስተኛው የሩሲያ–አፍሪካ ጉባኤ ላይ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአፍሪካ መሪዎችን ያስተናግዳሉ።
የክሬምሊን የውጭ ፖሊሲ ረዳት ዩሪ ኡሻኮቭ እንደገለጹት፤ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቅና ከተሰጣቸው 54 የአፍሪካ ሀገራት መካከል 48ቱ በስብሰባው ላይ ይሳተፋሉ።
ከእነዚህም ውስጥ 22ቱ በሀገር መሪዎቻቸው እንዲሁም ቀሪዎቹ በከፍተኛ ባለሥልጣናትና ሚኒስትሮች ደረጃ ይወከላሉ።
ይህም በአውሮፓውያኑ 2023 በሴንት ፒተርስበርግ ከተካሄደው ጉባኤ ጋር ተመሳሳይ የሀገራት ቁጥር ያለው ቢሆንም የታዳሚ መሪዎች ቁጥር ግን ከ17 ወደ 22 አድጓል።
በጉባኤው መርሐ ግብር መሠረት ሁለት የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባዎችና በፑቲን እና በተጋባዥ መሪዎች መካከል የሚደረጉ የሁለትዮሽ ውይይቶች ይካሄዳሉ።
በተጨማሪም ጥቅምት 19 ቀን የኮንፈረንሱ ተናጋሪ እና የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ከሆኑት የቡሩንዲ ፕሬዚዳንት ኤቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ ጋር ልዩ ውይይት ያደርጋሉ።
ከጉባኤው ጎን ለጎን የሩሲያ–አፍሪካ የኢኮኖሚና ሰብዓዊ ፎረም ይካሄዳል። የአፍሪካ ሕብረት፣ የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማኅበረሰብ (SADC)፣ የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ECOWAS)፣ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ፣ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና እና አፍሬክሲም ባንክን ጨምሮ ዋና ዋና ቀጣናዊ ተቋማት መሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸዋል።
ሩሲያ እና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ከአውሮፓውያኑ 2027 እስከ 2029 የሚዘልቅ አዲስ የጋራ የድርጊት መርሐ ግብር ለማፅደቅ አልመው እየሰሩ ይገኛሉ።
የመጀመሪያው የሩሲያ–አፍሪካ ጉባኤ በአውሮፓውያኑ 2019 በሶቺ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ባለው የሞስኮ ጉባኤ ወቅት የጋዝ ላኪ ሀገራት ፎረም ስብሰባም አብሮ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
በጌቱ ላቀው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: