በትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር አማካኝነት ሕዝቡ እስከ ታችኛው የመዋቅር እርከን ድረስ መሪዎቹን በነፃነት መመረጥ ጀምሯል።
በዚሁ መሠረት በደቡብ ምሥራቅ ዞን የደጉዓ ተንቤን ወረዳ ነዋሪዎች ያካሄዱት የባላደራ አመራር ምርጫ በነፃነትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተከናወነ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
በሕገ-ወጡ የሕወኃት ቡድን ደፍርሶ የቆየው የአካባቢው ሰላም በፌደራል መንግሥት ጥረት እንዲያገግምና በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የተደረገ ሲሆን፣ በዚህም መሠረታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ ሙሉ ሥራ ገብተዋል።
በፌደራል መንግሥት የተቋቋመውና የሥድስት ወራት የአገልግሎት ጊዜ ያለው የባላደራ አስተዳደር ዋና ዓላማ ሰላምን ማስፈንና ለቀጣይ ምርጫ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም መዋቅሩን እስከ ታችኛው እርከን የማሟላት ሥራ ተጠናክሮ እየተሠራ ይገኛል።
በምርጫው ሂደቱ ነዋሪዎች ያለምንም ጫና በነፃ መድረክ የቀረቡ፣ በትምህርት ደረጃቸውና በሕዝብ የተመሰገኑ አቅም ያላቸውን አመራሮች በራሳቸው ፍላጎት መምረጥ በመቻላቸው ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ከተመረጡት አመራሮች መካከል ወ/ሮ አዜብ ገብረሕይወት በማኅበራዊ ዘርፍ የተጎዱና የተቸገሩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ሲገልጹ፤ አቶ ገብረሕይወት አማኑኤል በበኩላቸው የሕዝቡን የሰላም ፍላጎት ለማረጋገጥ ከዞንና ከክልል አመራሮች ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
የባለአደራ አስተዳደር አመራር አደራጅ ቡድን አባል የሆኑት አቶ ማዕረግ ግርማይ፣ የትግራይ ሕዝብ ለረጅም ጊዜ ጠምቶት የነበረውን ነፃነት እና ዴሞክራሲ አግኝቶ በትምህርት ዝግጅታቸው ብቁ የሆኑና ለሕዝብ ተቆርቋሪ የሆኑ መሪዎችን በከፍተኛ ተነሣሽነት መምረጡን ተናግረዋል።
አሁን ላይ የሕዝቡን የመዋቅር፣ የመንግሥት አገልግሎት እና የጸጥታ ጥያቄዎች በፍጥነት ለመመለስ አዲስ የተመረጡትን አመራሮች ወደ ቀበሌ መዋቅሮች በማውረድ ሥራ እንዲጀምሩ የማድረግና የተሻለ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን የመሥራት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል።
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: