የአስተዳደር ጉዳዮች
ይህ ወር በታሪካችን ውስጥ ታላቅ ምዕራፍ የተመዘገበበት ነው፤ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ መሠረት አዲሱ የመደመር መንግሥት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም በይፋ ተመስርቷል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው አንደኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የካቢኔ አባላትን ሹመት በማጽደቅና የመንግሥት ኃላፊነት የላቀ ትጋት የሚጠይቅ መሆኑን በማጉላት ለሁለተኛው የሥራ ዘመናቸው ቃለ መሐላ ፈጽመዋል። በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያዘጋጀውን የምክክር አጀንዳ ለፌደራል እና ለክልል አካላት በይፋ አስረክበዋል። ይህን ታላቅ ሀገራዊ ስትራቴጂ ከግብ ለማድረስና ሁለንተናዊ ዝግጁነትን ለማጎልበት ከፍተኛ የመንግሥት አመራር አካላት በአካል ብቃት፣ በሥነ-ምግባር እና በዲሲፕሊን የሚያንጽ የወታደራዊ ሳይንስ ሥልጠና በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።
ማኅበራዊ ጉዳዮች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለመላው ኢትዮጵያውያን የኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ በዓሉ ሰላምን፣ የገዳ ሥርዓትን የሥልጣኔ መሠረቶችና የጋራ ብልጽግናን የሚያጎላ መሆኑን ገልጸዋል። “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን!” በሚል መሪ ቃል በተከበረው 19ኛው የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን ላይም ሰንደቅ ዓላማው የሉዓላዊነታችን መገለጫ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። አያይዘውም የዓድዋን ታሪካዊ ቅርስ በማስታወስ ዜጎች ለሀገራዊ አንድነት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። በመጨረሻም በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከኢቢሲ ጋር በትግርኛ ቋንቋ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የፕሮጀክት ማስጀመሪያ፣ ጉብኝትና ምርቃት
ጥቅምት ወር በሀገራዊ የኢንዱስትሪ፣ የመሠረተ ልማት እና የግብርና አቅም ግንባታ ረገድ ትልቅ እመርታ የታየበት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በዓመት 600 ቶን የማጣራት አቅም ያለውን ብሔራዊ የከበሩ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ መርቀዋል። በተጨማሪም ለሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የኢትዮጵያ ሚትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን እና የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽንን ጎብኝተዋል።
በክልሎች እና በከተሞችም የልማት እንቅስቃሴዎች ተፋጥነዋል። በጎንደር 185 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የመያዝ አቅም ያለውና ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚያለማው የመገጭ መስኖ ግድብ ተመርቋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በቆይታቸው የፋሲል ግቢንና የ«መሶብ» ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል። በአዲስ አበባ ደግሞ 351 ሄክታር መሬት ያረፈውና 10 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው የቀጨኔ–አምባሳደር–ጊዮን–ኢሬቻ–ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ተመርቋል። በተያያዘም የነዳጅ ፍጆታን ለመቀነስ በሀገር ውስጥ ከነዳጅ ወደ የተፈጥሮ ጋዝ (CNG) የተቀየሩ የመጀመሪያዎቹ 26 የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች በይፋ ሥራ ጀምረዋል፤ ይህም የትራንስፖርት ወጪን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስና የሕዝብ የጉዞ ታሪፍን በግማሽ ያቃለለ ነው።
ዲፕሎማሲ እና የሁለትዮሽ ግንኙነት
በዲፕሎማሲው ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን መድረኮች ጠንካራ ተሳትፎ አድርገዋል። የመደመር መንግሥት ምሥረታን ተከትሎ የደቡብ አፍሪካውን ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ እና የናይጄሪያውን ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሼቲማን በይፋዊ የሥራ ጉብኝት ተቀብለዋል። በተጨማሪም ከሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራህማንም ጃይሻንካር፣ ከእስራዔሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር ስትራቴጂካዊ ትብብሮችን ለማጠናከር የሚያስችሉ ውጤታማ ውይይቶችን አድርገዋል።
ቀጠናዊ ትስስርን ለማጠናከርም በኬንያው የ«ማሹጃ(የጀግኖች)» ቀን አከባበር ላይ ተገኝተዋል። በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው 12ተኛው የጣና ከፍተኛ የደህንነት ፎረም ከመጀመሩ አስቀድሞ ከኬንያው ምክትል ፕሬዚዳንት ኪቱሬ ኪንዲኪ እና ከሞዛምቢኩ ፕሬዚዳንት ዳንኤል ቻፖ ጋር ተወያይተዋል። በፎረሙ የመክፈቻ ንግግራቸውም አፍሪካውያን ሀገራት ውስጣዊ አቅማቸውን እንዲገነቡና በዓለም አቀፍ ሥርዓት ውስጥ አወንታዊ ዐሻራ እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሩን እንቅስቃሴያቸውን ያጠናቀቁት በሩሲያ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ነው። ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በንግድ፣ ጤና እና ኃይል ዙሪያ ተመካክረዋል። በ3ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ላይም ዘመናዊ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ከሩሲያ ጋር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ከቀድሞ ስምምነቶች አንጻርም ኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹን አሥራ ሁለት Su-35 ተዋጊ ጄቶች እና አራት የS-400 የአየር መከላከያ ባትሪዎችን ተረክባለች። በመጨረሻም የጠቅላይ ሚኒስትሩ «መደመር» መጽሐፍ የሩሲያኛ ዕትም በሞስኮ በይፋ መመረቁ የሀገሪቱ የፖለቲካና የአስተዳደር ፍልስፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተደራሽነት ይበልጥ ያሰፋ ሆኗል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: