የብሩንዲው ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ኢቫሪስት ንዳይሺሚዬ በሞስኮ በተካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ አፍሪካ በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ የጥሬ ዕቃ ምንጭ ብቻ ሆና መቅረት እንደሌለባት ገልጸዋል።
ታሪካዊ ወዳጅነት፣ የፀረ-ቀኝ ግዛት ትግል አንድነት እና እኩል መከባበር ላይ በተመሰረተው በዚህ ጉባኤ ላይ ፕሬዝዳንቱ እንደተናገሩት፣ አህጉሪቱ የተፈጥሮ ሀብቷን፣ የግብርና አቅሟን እና ወጣቶቿን በማስተባበር የምርት፣ የእድገት እና የፈጠራ ሥራዎች እውነተኛ ተዋናይ በመሆን በራሷ እግሮች ላይ መቆም አለባት።
አህጉሪቱ ያለባትን የንግድ፣ የፋይናንስ፣ የአካባቢ እና የሰብዓዊ ተግዳሮቶች ለመሻገር ተጨባጭና የተቀናጀ ምላሽ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ፕሬዝዳንት ንዳይሺሚዬ፤ አሁን ባለው አስቸጋሪ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ ምንም ዓይነት ሀገር ወይም አህጉር ብቻውን ሊቆም እንደማይችል አጽንኦት ሰጥተዋል።
በጉባኤው ላይ የተገኙት የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው፣ የአፍሪካ ሀገራት የወጪ ንግድ አዲስ ዓይነት የቅኝ-ግዛት መቆጣጠሪያ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።
ተፅዕኖ ፈጣሪውን የቀድሞ የቡርኪናፋሶ መሪ ቶማስ ሳንካራ "ዕዳ አዲሱ ቀኝ ግዛት ነው፤ ቀኝ ገዢዎች እራሳቸውን የቴክኒክ አማካሪ በሚል ስያሜ የሸፈኑበት ሥርዓት ነው"ያሉትን ንግግር ያወሱት ፑቲን፣ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን እና በሀገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ሙከራዎችን መቀልበስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአህጉሪቱ መካከል ያለው ንግድ ከጠቅላላው የንግድ ልውውጥ 15 በመቶ ብቻ የሆነው የቀደሙት መሠረተ ልማቶች ጥሬ ዕቃን ወደ ውጭ ለመላክ ታስበው የተዘረጉ በመሆናቸው እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ አመልክተዋል።
አያይዘውም ሩሲያ የአፍሪካን የዕዳ ጫና ለማቃለል ያደረገችውን እርምጃ በማንሳት፣ አህጉሪቱ በዓለም አቀፍ ውሳኔዎች ላይ ያላትን ተሳትፎና የልማት እንቅስቃሴ መደገፏን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: