የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቦሌ ክፍለ ከተማ የተገነባውን የቦሌ ሹቡ ኤጀርሳ የጋራ መኖሪያ መንደር ለልማት ተነሺዎች ዛሬ በይፋ አስተላልፈዋል።
በስነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባዋ፣ አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ምቹ እየሆነች ከመምጣቷ ባሻገር በሰው ተኮር የልማት ሥራዎቿ ዓለም አቀፍ እውቅናን እያገኘች መሆኑን ገልጸዋል።
የከተማዋ የዘመናዊነት ግንባታ ሂደት የነዋሪዎች የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባዋ፣ ነዋሪዎች ለልማት በመነሳት ለከተማዋ ዕድገት እያበረከቱ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ለልማት ተነሺዎች ከዚህ ቀደም ይኖሩበት ከነበረው የተሻለ የኑሮ ሁኔታ እንዲኖራቸው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ያመለከቱት ከንቲባ አዳነች፤ ዛሬ የተላለፉት መኖሪያ ቤቶችም የማኅበራዊ ትስስራቸው ሳይናጋ አብረው የሚኖሩበትና በዘመናዊ መልኩ የተገነቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ነዋሪዎቹ የተሰጣቸው መኖሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን ዘላቂ የገቢ ምንጭ እንዲሆናቸው በማሰብ የከብቶች ማድለቢያ፣ የወተት ላሞች ማርቢያ፣ የመኖ ማቀነባበሪያ እንዲሁም የግብርና ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡበት ዘመናዊ ሱቆች ተገንብተው ከተለዋጭ ቤቶቹ ጋር ተላልፈዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ አክለውም፣ የአዲስ አበባ የልማት እንቅስቃሴ ሁሉ ሰው ተኮር በመሆኑ ወደፊትም በከተማዋ በሚከናወኑ የዘመናዊነት ግንባታዎች ውስጥ ለልማት ተነሺዎች የተሻለ የኑሮ ዕድል የመፍጠሩ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።.
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በባዬ ሙላት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: