“የረሃብ መከታው እንሰት” በስቴሮይድ የበለጸገ ሙዝ እና ድንቅ ሰብል ከሚሉት እጅግ አሞጋሽ ቅጽል ስሞቹ ጋር የሚወዳደር ጥቂት ነው።
ሆኖም ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ከሆነ የእፅዋቱን የተለመደ ስም እንሰት የሚለውን ሰምተው የማያውቁበት ዕድል እጅግ የሰፋ ነው።
በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ ከ20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ዋና ምግብ በመሆን የሕይወት ዋስትና የሰጠው እስከ 10 ሜትር ወይም 33 ጫማ ቁመት ማደግ የሚችለው ይህ ተክል፤ የዓለምን የካሎሪ ፍላጎት ከግማሽ በላይ የያዙትን እንደ ሩዝ፣ ስንዴ እና በቆሎ ያሉትን “ሶስቱን ታላላቅ” ሰብሎች ሲነጻጸር ዓለም አቀፍ ዝናው አነስተኛ መሆኑ ያስገርመኛል ይላል እንግሊዛዊው ጀምስ ቦሬል።
ባዮሎጂስቱ ጀምስ ቦሬል የእንሰትን ባህሪያት በጥልቀት ለማጥናት ዕድል እንዳገኘ በመግለጽ ይህ ተክል ለአፍሪካና ለዓለም የምግብ ዋስትና እጦት ትልቅ መፍትሔ ሊሆን እየቻለ አነስተኛ ግምት ማግኘቱ በእጅጉ የሚያበሳጭ እና የሚያስገርም መሆኑን ይገልጻል።
ሁሉን ያያዘ፣ ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ፣ ድርቅንና በሽታን የሚቋቋም በመሆኑ 60 የእንሰት ተክሎች ብቻ አምስት አባላት ያሏቸውን ቤተሰብ ለአንድ ዓመት ሙሉ መመገብ የሚችልበት አስደናቂ አቅም አለው ይለናል።
ከዚህም በላይ በየዓመቱ እንደገና መዘራት ሳያስፈልገው ከሁለት ዓመት በላይ ሊበቅልና ሊኖር የሚችል የብዙ ዓመት ሰብል ነው።
ጀምስ ቦሬል ከባልደረቦቹ ጋር አብሮ ባዘጋጀው የ2021 የቀጠናው የናሙና ጥናት መሠረት እንሰት በጣም ተላማጅና ለአየር ንብረት ተስማሚ በመሆኑ በደቡብና ምዕራብ አፍሪካ ሰፊ ቦታዎች ላይ ሊመረት ይችላል።
በአሁኑ ወቅት ያለው የማልማት አቅሙ እስከ 12 እጥፍ ሊሰፋ የሚችል ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ የግብርና ምርት ዕድገት ቢኖርም የምግብ ዋስትና እጦት እየጨመረ በሚገኝበት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ተጨማሪ 111.5 ሚሊዮን ሰዎችን መመገብ እንደሚችል በጥናታችን አረጋግጠናል ይላል።
በአውሮፓውያኑ 2017 በምዕራብ እንግሊዝ በሚገኘውና 17,000 የሚጠጉ የእፅዋት ዝርያዎችን በያዘው በኪው ሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ መስራት ሲጀምር ግን ስለ እንሰት ሰምቶ እንደማያውቅ በመገረም ይናገራል።
የዱር እንሰት ከሰሜናዊቷ ሱዳን ጀምሮ እስከ ሞዛምቢክ ድረስ ባሉ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በጥቂቱ ቢገኝም ሰብሉ ጥቅም ላይ የሚውለው ግን ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ መሆኑ ግልጽ እንደሆነለትም ይገልጻል።
በኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ ደጋማ አካባቢዎች ከባህር ወለል በላይ ከ1,500 እስከ 3,000 ሜትር ከፍታ ባለው ቦታ ላይ ገበሬዎች ከማዕከላዊው ግንዱ እስከ 5 ሜትር ርዝመት ያላቸው አረንጓዴ ቅጠሎች የሚያወጡትንና በስህተት ዛፍ ሊመሰሉ የሚችሉትን ተክሎች በመስመር ተክለው ይንከባከባሉ።
እንሰት ዛፍ ሳይሆን እንጨት የሌለው ግዙፍ ዕፅዋት ሲሆን ግርማ ሞገሱ ከታዋቂው የሙዝ ዘመዱ ጋር በመመሳሰሉ “ሐሰተኛ ሙዝ” በመባል ይታወቃል።
ከሶስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚገኘው ድብልቅ ቆጮ በመባል የሚታወቀውን ኢትዮጵያውያን ዋና ምግብ ለማዘጋጀት ይውላል፤ በመፍጨት ሂደቱ የሚገኘው ተረፈ ምርት ቡላ ደግሞ ከስታርች የበለፀገ ጭማቂ ተጨምቆ ለገንፎና ለዱቄት ምግቦች ያገለግላል።
እንሰት ሰፊ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅም ያለው መሆኑን በኪው ጋርደንስ በሞቃታማ አካባቢ በተደረገ ሙከራም እንደተረጋገጠ ተናግሯል።
ታዲያ እንሰት በአንድ የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ያን ያህል ስኬታማ ከሆነ ለምን በሌሎች ቦታዎች ላይ ብዙም አልተስፋፋም? እያለ የሚጠይቀው እንግሊዛዊው ተመራማሪ ወደ ኬንያ፣ ታንዛኒያ ወይም ኡጋንዳ ሄደህ ይህ እንደሚበላ ታውቃለህ? ብለህ ስትጠይቅ ሰዎች በመገረም ያዩሃል እያለ እሱም መገረሙን ይገልጻል።
እንደ ቦሬል መላምት ግን ይህ ሰብል ከኢትዮጵያ ውጭ ብዙም እንዳይታወቅ የሆነው አንድም ኢትዮጵያ የባዮ-ወረራን ለመከላከል የእፅዋት ዝርያዎችን ዓለም አቀፍ ዝውውር በጥብቅ ስለምትቆጣጠር አሊያም እንሰት በአብዛኛው በሴት ገበሬዎች የሚከናወንና ከፍተኛ ጉልበት የሚጠይቅ ሥራ መሆኑ፣ እንዲሁም ወደ ምግብነት ለመቀየር ልዩ እውቀትን እና ልምድ የሚጠይቅ ጣዕም ያለው በመሆኑ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች።
እናም ኢትዮጵያ በእቅፋ ይዛው ለዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ሊተርፍ የሚችል እውነተኛ የምግብ ዋስትና መፍትሔ ይዛ መቅረቧ ታሪካዊ ድል ነው።
“እንሰት በጣም ጥሩ ነው፣ እናንተ ኢትዮጵያውያን በዓለም ላይ እንሰት ያላችሁ ብቸኛ ሕዝብ ናችሁ፤ እኛ በእንሰት ፍላጎት አለን፣ ሰብሉ ድንቅ እንደሆነ እናስባለን፣ አነስተኛ መሬት በመጠቀም የተሻለ እርሻ እንድታመርቱና የተሻለ ገቢ እንድታገኙ የሚያስችል እድል ይዛችኋል” በማለት ተናግሯል የሥነ ሕይወት ተመራማሪው ጀምስ ቦሬል።
በመሀመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: