Search

አስገራሚው የሞባይል መተግበሪያዎች ዕድገት

ስልክዎ ላይ ምን ያክል መተግበሪያዎች አለዎት? የስልክዎን መረጃ መጫኛ ቦታ የማያጣብቡ አነስተኛ ሜጋ ባይት ያላቸው እና ፈጣን የሆኑ መተግበሪያዎች ተመራጭ እየሆኑ ነው።

በአፕል ኩባንያ አማካኝነት በቅድሚያ የተዘጋጁት የስልክ መተግበሪያዎች ብዙም ውስብስብ ያልሆኑ እንደ ካልኩሌተር፣ ሰዓት፣ ኢሜል እና ካላንደርን መጠቀም የሚያስችሉ ነበሩ።

ዛሬ ላይ ደግሞ የሰው ልጅ ከመተግበሪያዎች ጋር ያለው ቁርኝት እጅጉን የጠበቀ በመሆኑ ዘመናዊ አገልግሎትን የሚሰጡ መተግበሪያዎች በልጽገዋል።

በተለይ በሰለጠነው ዓለም ያነዘመናዊ መተግበሪያዎች የእለት ከእለት ሕይወትን ማስኬድ እየከበደ መጥቷል።

የምግብ ትእዛዞችን ለመላክ፣ የእለቱን የአየር ሁኔታ ለማወቅ፣ የስቶክ ማርኬትና የገበያ ዋጋዎችን ለመገንዘብ፣ የአየር ትኬት ለመቁረጥ፣ የዓለምን ውሎና አዳር ለማወቅ፣ ከዚህም በላይ የጤና ሁኔታን እና የሕክምና ቀጠሮን እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሞባይል መተግበሪያዎችን መጠቀም አስፈላጊ ሆኗል።

በአማካይ የሞባይል ስልክ የሚጠቀሙ ሰዎች እስከ አርባ የሚደርሱ የተለያዩ መተግበሪያዎችን በስልካቸው ላይ የሚጭኑ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ ቢያንስ ዘጠኝ የሚሆኑትን መተግበሪያዎች በየቀኑ እንደሚጠቀሙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በዚህ መንገድ የተጀመረው ቴክኖሎጂ እያደገ፣ አይነታቸውም እየበዛ መጭቷል። የመጀመሪያዎቹን ስማርት ስልኮች ወደገበያ መምጣት ተከትሎ ነበር የሞባይል መተግበሪያዎች መዘጋጀት የጀመሩት።

በኋላም ጉግል ፕሌይ ስቶርን መስርቶ የተለያዩ የአንድሮይድ መተግበሪያዎችን አዘጋጅቶ ማቅረብ ጀመረ። ዛሬ ላይ በየቀኑ በሺህ የሚቆጠሩ የተለያየ ጥቅም ያላቸው መተግበሪያዎች እየተሰሩ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። አሁን ላይ አጠቃላይ የመተግበሪያዎች ቁጥር ከ5 ሚሊዮን ልቋል።

ከእነዚህ የሞባይል መተግበሪያዎች ውስጥ በቁጥር የሚልቁት የጌም መተግበሪያዎች ሲሆኑ፤ የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች፣ የትምህርት፣ የመረጃ እና የዜና መረጃዎችን የሚያቀርቡትም ይገኙበታል።

በዓለም ላይ ካሉት መተግበሪያዎች 90 በመቶው ሰዎች በነፃ እንዲጠቀሙባቸው በአፕ ስቶር እና ፕሌይ ስቶር ላይ ለስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች ይቀርባሉ።

የተለያዩ ተቋማት አገልግሎታቸውን በመተግበሪያ አማካኝነት በቀላሉ ያቀርባሉ። አሁን አሁን የዓለማችን ታላላቅ የዜና እና የመረጃ ተቋማት መረጃቸውን ለማድረስ እራሱን የቻለ የሞባይል መተግበሪያ አዘጋጅተው ያጠቀማሉ።  

በዚህም መሰረት የዜና አቅራቢ ተቋማት በአፕል ስቶር ላይ 38 ሺህ፣ በፕሌይ ስቶር ደግሞ 42 ሺህ የሚደርሱ መተግበሪያዎችን አሰርተው ጥቅም ላይ አውለዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንም ከዘመኑ ጋር ለመዘመን እያደረገ ያለው ጥረት አንዱ አካል የሆነውን መረጃዎችን በሞባይል መተግበሪያ ለማቅረብ የሚረዳውን መተግበሪያ አበልጽጓል። “EBC” የተሰኘው መተግበሪያ በአፕል ስቶር እና በፕሌይ ስቶር ላይ  ተጭኖ ጥቅም ላይ ውሏል።

በዚህ አዲስ የሞባይል መተግበሪያ አማካኝነትም ወቅታዊና የቀጥታ ስርጭቶች፣ እለታዊ ዜናዎች፣ ድራማ እና የተለያዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን በቀላሉ መከታተል ይቻላል።

በጥቅም ላይ የዋለውን የሞባይል ስልክ መተግበሪያ በመጫን የኢቢሲን ወቅታዊ ዜና እና መረጃዎችን እንዲሁም የመዝናኛ ፕሮግራሞችን እንዲደርስዎት ያድርጉ።