በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢንዶ ቶሺያኪ የተመራ የጃፓን የፓርላማ ልዑክ ቡድንን ተቀብሎ ውይይት አደረገ።
ውይይቱ ኢትዮጵያ እና ጃፓን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በውይይቱ የጃፓን ልዑክ ቡድን መሪ ኢንዶ ቶሺያኪ፤ ይህ ዓይነቱ መድረክ የቆየውን የኢትዮጵያን እና የጃፓንን ወዳጅነት በተለያዩ ዘርፎች ለማጠናከርና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል።

ጃፓን፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሁለተኛውን ግዙፍ የሕዝብ ቁጥር የያዘችና በዕድገት ጎዳና ውስጥ ያለች ሀገር እንደመሆኗ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንዲሁም የዓለም የንግድ ማኅበር አባል ለመሆን ለምታደርገው ጉዞ ድጋፏ ይቀጥላል ብለዋል።
ኢንዶ ቶሺያኪ ኢትዮጵያም የሴቶችን ተሳትፎና የአስተዳደር አካል በማድረግ እየሰራች ያለችበት ሂደት የሚደነቅ መሆኑን መግለጻቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እና ጃፓን የሁለቱ ሀገራት ረጅም ዓመታት በዲፕሎማሲ ፣ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ረጅም ታሪክ ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አስታውሰው፤ ለጋራ እድገት እና ብልፅግና የሚጠቅሙ መልካም ግንኙነቶች የበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ የቆየው የኢትዮጵያ እና ጃፓን ግንኙነትና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር በማደግ በንግድ ፣ በልማት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸው ትስስር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መምጣቱንም አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም በማከናወን በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ በርካታ ዕድገትን እያስመዘገበች እንደምትገኝ ለልዑካን ቡድኑ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በርካታ ሥራዎችን ማከናወኗን የገለጹት ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ፤ በዚህ ረገድ ጃፓን በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላት ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከጃፓን ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነትን በመጀመር ረገድ ቀዳሚ አፍሪካዊት ሀገር መሆኗ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረጓም በውይይቱ ወቅት ተመላክቷል።