Search

አረንጓዴው ወርቅ - ከችግኝ እስከ ቢሊዮን ዶላር!

ሰኞ ሰኔ 08, 2018 65

ስለ ካርበን ሽያጭና ዛፍ መትከል ስለሚያስገኘው የቢሊዮን ዶላሮች የኢኮኖሚ ምንጭ ማወቅ የአሁኑ ዘመን የህልውና እና የብልጽግና መሠረትን ለመረዳት ወሳኝ መነሻ ነው።

ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ላይ የምናኖረው እያንዳንዱ አረንጓዴ አሻራ፣ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ከመቋቋም ባለፈ ታላቅ ሀገራዊና አህጉራዊ ፋይዳ አለው።

ሀገራችን በይፋ የነደፈችውን የ50 ቢሊዮን ችግኞች ተከላ ግዙፍ ራዕይ ሙሉ በሙሉ እውን ለማድረግ የዘንድሮዉ ክረምት ብቻ ቀርቷታል።

ይህ ታሪካዊ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት እንዴት እንደሚያሳድገውና አዲስ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ምዕራፍ እንደሚያበስር በጥልቀት መፈተሽ ተገቢ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ዘመናት እጅግ ሰፊና ማራኪ የደን ሽፋን የነበራት ሀገር እንደነበረች የታሪክ ድርሳናት ያረጋግጣሉ።

ሆኖም ግን ባለፉት አያሌ አሥርት ዓመታት በሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ በእርሻ መሬት መስፋፋት እና በሕገ-ወጥ የደን ምንጣሮ ምክንያት ይህ ውድ የሀገር ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ ተመናምኖ መቆየቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው።

ይህ የተፈጥሮ መራቆት ሀገራችንን ለአደጋ ለጋሽ የድርቅ አዙሪት፣ ለአፈር መሸርሸርና ለግብርና ምርታማነት መቀነስ አጋልጦ የኖረ ሲሆን፣ ለሕዝባችን የኑሮ ዋስትናም ትልቅ ፈተና ደቅኖ ቆይቷል።

ይህንን ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ቀውስ ከመሠረቱ ለመቀልበስና የነገዋን አገር በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት «የአረንጓዴ አሻራ» የተሰኘ ግዙፍ ብሔራዊ ንቅናቄ ተበሰረ።

ይህ ንቅናቄ ጊዜያዊ ዘመቻ ሳይሆን የሀገርን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስን እና ጊዜውን የዋጀ መርሐ ግብር ሆኖ ቀጥሏል።

እስከ አሁን ባለው ሂደት ብቻ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተተከሉ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥን ለመመከት በምታደርገው ጥረት የዓለም ቀዳሚ ተዋናይ አድርጓታል።

በዚህ ግዙፍ ሀገራዊ ንቅናቄ እየተተከሉ ያሉ መሠረታዊ የልማት ችግኞች የደን ዛፎችን ብቻ ያካተቱ አይደሉም።

ይልቁኑ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውንና የምግብ ዋስትናን በተግባር የሚያረጋግጡ የፍራፍሬ ዝርያዎችን እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ አፕል እንዲሁም የቡና እና የሻይ ቅጠልን ያካተቱ በመሆናቸው የአርሶ አደሩን የኑሮ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀየሩ ይገኛሉ።

ከተከላው ጎን ለጎን ችግኞችን በማፍላትና በመንከባከብ ሂደት ውስጥ ለሚሊዮኖች በተለይም ለሴቶች እና ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

እነዚህ የፍራፍሬ ምርቶች ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እና ለውጭ ኤክስፖርት ከመዋል ባለፈ፣ ለሀገር በቀል የአግሮ-ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ወሳኝና ዘላቂ የጥሬ ዕቃ ግብዓት በመሆን ላይ ናቸው።

ይህ ታላቅ ንቅናቄ ከአየር ንብረት ጥበቃ እና ከምግብ ዋስትና ባሻገር፣ ሌላ እጅግ ግዙፍና እስካሁን በስፋት ያልተመዘመዘ «የተደበቀ ሀብት» ይዟል፤ እርሱም ዓለም አቀፉ የካርበን ሽያጭ (Carbon Market) ነው።

የካርበን ገበያ ማለት በካይ ጋዞችን ወደ ከባቢ አየር የሚለቅቁ የበለጸጉ ሀገራትና ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኢንዱስትሪዎች፣ ይህንን ልቀታቸውን የሚያካክስላቸውን እና ካርበንን የሚመጡ ደኖችን ለሚያለሙ ሀገራት በቀጥታ የገንዘብ ክፍያ የሚፈጽሙበት ዓለም አቀፋዊ የፋይናንስ ሥርዓት ነው።

በአረንጓዴ አሻራ የምንተክላቸው ቢሊዮን ዛፎች ከከባቢ አየር ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው በካይ ጋዝ የመምጠጥ እና የማከማቸት አቅም ስላላቸው፣ ለሀራችን አዲስ እና ዘላቂ የዶላር መገኛ መስመር እየከፈቱ ይገኛሉ።

 ለዚህ ተግባራዊ ስኬት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘውን የ«ሁምቦ ማኅበረሰብ የደን ልማት ፕሮጀክት» በዓይነተኛ ማሳያነት መጥቀስ ይቻላል።

ይህ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ተራቁቶ እና ደርቆ የነበረን ተራራማ አካባቢ በማኅበረሰቡ አጋዥነት መልሶ በማልማት፣ በአፍሪካ ደረጃ በዓለም ባንክ የካርበን ፈንድ ዕውቅና ያገኘ ቀዳሚው ሀገራዊ ስኬታችን ሆኗል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ከተፈጥሮ መታደስ ባለፈ ከካርበን ሽያጭ በቀጥታ የገንዘብ ተጠቃሚ መሆን ችሏል።

በአሁኑ ወቅት መንግሥት ይህንን የሁምቦን ተለይቶ የታወቀ ስኬት ወደ ሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋት ሰፊ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎችን አዘጋጅቶ፣ የካርበን ክምችት ልኬትና ምዝገባን በዘመናዊ መንገድ እያከናወነ ይገኛል።

የዚህን ዘርፍ ስፋት እና ጥልቀት በቁጥር ስናስደግፈው ይበልጥ ግልጽ ይሆናል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከዓለም ባንክ ጋር የ40 ሚሊዮን ዶላር የካርበን ሽያጭ ውል የተፈራረመች ተፈራርማለች፡፡ ከኖርዌይ መንግሥት ጋር ደግሞ በካርበን ክሬዲት አማካኝነት ወደ ገንዘብ የሚቀየር የ75 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ፈጽማለች።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የካርበን ገበያ ከ107 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚንቀሳቀስበት ግዙፍ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው።

እንደ ብራዚል ያሉ ሀገራት ከዚህ ዘርፍ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ፣ ኢንዶኔዥያ ደግሞ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ ማግኘት ችለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ ልማት ጥረት አጠናክራ ስትቀጥል ከዚህ ዓለም አቀፍ የገበያ ፈንድ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ በመውሰድ የውጭ ምንዛሬ አቅሟን ማሳደግ ትችላለች።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከሀገራዊ ፋይዳው ባሻገር፣ የኢትዮጵያን ስልታዊ የውጭ ፖሊሲ እና ቀጣናዊ ትስስር የሚያጠናክር የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ መሣሪያ ሆኗል።

ሀገራችን ለጎረቤት አገራት ለጂቡቲ፣ ለኬንያ፣ ለሶማሊያ እና ለደቡብ ሱዳን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በነፃ በማካፈል፣ በጋራ የመልማትና ድንበር ተሻጋሪ የተፈጥሮ ሀብትን በጋራ የመጠበቅ ራዕይን በተግባር አሳይታለች።

ይህ በጎ ተግባር ቀጣናዊ ሰላምን እና ትብብርን የሚሸከም የህልውና መሠረት ነው። ድሮ በድርቅ እና በረሃብ ስሟ ይነሳ የነበረችው ሀገራችን ዛሬ ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ቀውስ መፍትሔ አምጪ ሆና ብቅ እንድትል አድርጓታል።

በዚህም ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ፍትሕ አንቀሳቃሽ ሞተር በመሆን፣ የበለጸጉ ሀገራት ለአፍሪካ የአየር ንብረት ፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉ በሞራል የበላይነት የምትጠይቅበትን አቅም ፈጥራለች።

በተጨማሪም የአረንጓዴ አሻራ ልማት እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እና ግዙፍ የሃይድሮ-ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎቻችንን ደኅንነት ለመጠበቅ የላቀ አስተዋጽኦ አለው።

በተፋሰሶች አከባቢ የሚተከሉ ዛፎች የአፈር መሸርሸርን በመግታት ግድቦቻችን በደለል እንዳይሞሉ እና የአገልግሎት ዘመናቸው እንዲረዝም ያደርጋሉ።

ይህ ስኬት ሊመዘገብ የቻለው ደግሞ ቀድሞ በሴፍቲኔት እና በግዴታ ይሠራ የነበረው የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ፣ ዛሬ በማኅበረሰቡ ሙሉ ፈቃደኝነት እና የባለቤትነት ስሜት በመተካቱ ነው።

በአካባቢ ጥበቃ ሳይንስ ውስጥ «ያለ ሕዝብ ተሳትፎ የሚተከል ዛፍ፣ ያለ ውኃ እንደተተወ ችግኝ ነው» እንደሚባለው ሁሉ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ የሕዝብን ንቁ ተሳትፎ ማረጋገጥ በመቻሉ የችግኞቻችን የመጽደቅ ምጣኔ ከ80 በመቶ በላይ ሊያድግ ችሏል።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተራ ዛፍ ከመትከል ተግባር በእጅጉ የላቀ፣ ሀገራዊ ብልጽግናን ከዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ጋር ያስተሳሰረ ታላቅ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።

ይህ ንቅናቄ በተፈጥሮ የተቸረንን ምቹ የአየር ንብረት እና መልክዓ-ምድር በአግባቡ በመጠቀም፣ ለተተኪው ትውልድ የሚበቅል፣ የሚለምልም እና የሚጠቅም ሕያው ቅርስ እና የማያረጅ ውርስ ጥሎ የሚያልፍ የአዲሱ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታችን ማሳያ ነው።

በበረከት ሽመልስ