Search

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በጁባ ለሚያከናውነው የዘመናዊ ቤቶች ግንባታ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቅቋል

ሰኞ ሰኔ 08, 2018 67

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በጁባ ከተማ ለሚያከናውነው የዘመናዊ ቤቶች ግንባታ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የደቡብ ሱዳን መንግሥት ገለጸ።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በጁባ የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችለውን ስምምነት አድርጓል።
ቀደም ሲል በአዲስ አበባ የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ወደ ተግባር የሚያስገባው ይኸው አዲስ ውል በጁባ ከተማ ተፈርሟል።
የህንጻ ግንባታ ሳይቶች መረጣ እና ተያያዥ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች አፈጻጸም በደቡብ ሱዳን ሴንተራል ኢኳቶሪያል ግዛት የኮንስትራክሽን እና ቤቶች ኮርፖሬሽን በቀረበ የጥናት ሪፖርት አማካኝነት በዝርዝር ተገምግሟል።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል (ዶ/ር) እና የግዛቱ አስተዳዳሪ ኢማኑኤል አድል ስምምነቱን ፈርመዋል።
በስምምነቱ መሠረት ኮርፖሬሽኑ በጁባ ከተማ ዘመናዊ የንግድና የመኖሪያ ሕንጻዎችን የሚገነባ ይሆናል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል (ዶ/ር) ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ አዱት ኪር ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ላይ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሊል ከድር እና በደቡብ ሱዳን በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩት ታዋቂው ባለሀብት አይሸሽም ተካ (ዶ/ር) ተገኝተዋል።
ልዩ መልዕክተኛ አዱት ኪር ኮርፖሬሽኑ በጁባ ከተማ ለሚያካሂደው የቤት ልማት ፕሮግራም የደቡብ ሱዳን ፌዴራል መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
የቤት ግንባታው መጀመር በሁለቱ እህትማማች ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ያላቸውን ሙሉ እምነት በመግለጽ፣ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ለስምምነቱ ተግባራዊነት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ረሻድ ከማል (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በደቡብ ሱዳን የቤት ልማት ዘርፍ የተሰማራው የጋራ ተጠቃሚነትን፣ አብሮነትን እና ወንድማማችነትን መርህ አድርጎ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ አጠናቅቆ በቅርቡ ግንባታውን በይፋ እንደሚጀምር አስታውቀዋል።
በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል (ዶ/ር) የተመራው የልዑካን ቡድን ለ4 ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን የሥራ ጉብኝት አጠናቅቆ ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል።