የግዙፉ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ የአገልግሎት ዘርፍ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም በጎበኙበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ የፕሮጀክቱ ግንባታ የሀገራችንን ገጽታ እና ሀብት በከፍተኛ ደረጃ ከማበልጸግ ባሻገር ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ ጠንካራ መሠረት እየጣለ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከፍተኛ የአገልግሎት ኢንዱስትሪን ወደ ሀገራችን በመሳብ ግዙፍ የኢኮኖሚ መነቃቃት እንደሚፈጥር በንግግራቸው ጠቁመዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው መገንባት አውሮፕላኖችን ከማስተናገድ ባለፈ፣ ከሚመጣው እና ከሚሄደው መንገደኛ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ሀብት የሚንቀሳቀስበት ማዕከል እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ሙሉ ትርጉም የሚያገኙት እና ሀብቶቻችን አግባብነት ያለው ምላሽ የሚያመጡት አውሮፕላን ማረፊያው በውጤታማነት ሲጠናቀቅ መሆኑን አመላክተዋል።
"ብዙዎች ወደ ሀገራችን ሲመጡ፣ ሲውሉ፣ ሲያድሩ የተለያዩ ምርት እና አገልግሎቶችን ሲጠቀሙ፣ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት የሚቀይር ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ" በማለትም የፕሮጀክቱን ሰፊ ጠቀሜታ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት 8 ሺህ ሰዎችን የቀጠረው ፕሮጀክት፣ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ በሚገባበት ጊዜ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ዜጎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን ታምኖበታል።
ይህን መሰል ሜጋ ፕሮጀክቶችን አልቆ ማሰብ፣ ፈጥኖ መጀመር እና በጥራት መጨረስ ኢትዮጵያ አሁን የጀመረችው አዲስ እና ጠቃሚ ልምምድ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ይህ ጊዜ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ጊዜ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህን ወርቃማ ዕድል በመጠቀም እና ሀሳብን ወደ ተግባር በመተርጎም የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
አክለውም፣ "ይህ ዕድል ካመለጠን ወደፊት መልሶ ለማሰብም ሆነ ለመሥራት እጅግ አስቸጋሪ ስለሚሆን፣ ሁላችንም ትልቁን ምስል አይተን ልንሠራ ይገባል" ብለዋል።
በለሚ ታደሰ