በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ የሚገኘው እና የወላይታዎች መገለጫ የሆነው የዳሞታ ተራራ እንዲለማ ኅብረተሰቡ ለረጅም ጊዜ ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል።
ተራራው የተለያዩ የብዝኃ ሕይወት መገኛ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው መስህብ ስፍራዎች የሚገኙበት ነው።
በመሆኑም ተራራውን ማልማት በአካባቢው የቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
እንደ ሀገር በተጀመረው የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማልማት እና የማሳደግ ኢኒሼቲቭ አካል በማድረግ የዳሞታ ተራራን የማልማት ተግባር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ይገኛል።
በዚህም እስከ ተራራው ጫፍ በመድረስ በተራራው ላይ የሚገኙ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቦታዎችን ለመጎብኘት የሚያስችሉ 7 ሺህ 187 መወጣጫ ደረጃዎችን የመገንባት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
ከ5.34 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝመው ይህ ፕሮጀክት፣ በውስጡ ታሪካዊውን የሞቼና ቦራጎ ዋሻ፣ የዳሞታ ካርበን ፕሮጀክትን፣ በተራራው ጫፍ የምትገኘውን የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን፣ ከተራራው የሚፈልቁ የውኃ ምንጮችን እና ሰባቱን የዳሞታ ተራራ ሰንሰለቶች በማካተት ነው እየተገነባ የሚገኘው።
የዳሞታ ተራራ 12 ሺህ 500 ሔክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን፣ ከባሕር ጠለል በላይ 2 ሺህ 750 ሜትር ከፍታ እንዳለው እና ዙሪያው ከ68 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት እንደሚሸፍን ይነገራል።
እንደ ሀገር የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ማልማት እና የቱሪዝም ሀብትን የማበልጸግ ስትራቴጂ ትኩረት ተሰጥቶታል።
በትዕግሥቱ ቡቼ