Search

የአረንጓዴ ዐሻራ ብሔራዊ ሥራችን ከተፈጥሮ የመታረቅ፣ በልማት የመላቅ አዲስ ጎዳና ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ሰኞ ሰኔ 08, 2018 53

የአረንጓዴ ዐሻራ ብሔራዊ ሥራችን ከተፈጥሮ የመታረቅ፣ በልማት የመላቅ አዲስ ጎዳና ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

የአረንጓዴ ዐሻራ ብሔራዊ ሥራችን ከተፈጥሮ የመታረቅ በልማት የመላቅ አዲስ ጎዳና ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አንደገለጹት፣ ለአንዲት ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሕዝብ ተደምረን በሠራነው የአረንጓዴ ዐሻራችን፣ ልምላሜ የተራቡ ተራሮች አረንጓዴ ለብሰዋል፤ ምንጮች እና ተፋሰሶች ምድሩን አረስርሰዋል።

በረሃማነት ይጸናባቸው የነበሩ ክበበ ምድሮች ነፋሻማ ሆነዋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የተፈጥሮን ጫና ተቋቁመናል! ይህ ደግ የተፈጥሮ ዕርቅ ነው ብለዋል።

የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥን ከተፈጥሮ ጥበቃ ጋር በማስተሣሠር በተሠራው ሥራ የፍራፍሬ ተክሎች በስፋት መልማታቸውንና ፍሬ መስጠት መጀመራቸውንም አመልክተዋል።

ይህም በምግብ ራስን ለመቻል ለጀመርነው ብሔራዊ ኢኒሼቲቭ ተደማሪ ዐቅም ሆኗል ነው ያሉት።

አረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያ ልጆች ከፖለቲካ አሰላለፍ አልፈው፣ ከሐሳብ ተቃርኖ ተሻግረው፣ ገጸ ብዙ ልዩነቶችን አሸንፈው ለሀገርና ለትውልድ አስበው ያሳኩት የመተባበር ድል፣ የተጨበጠ ማሳያ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ልጆች ስንተባበር ትርፋችን እልፍ፣ ዕቅዳችንም የተሳካና የሠመረ ይሆናል ብለዋል።

የዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ የእስከ ዛሬ ድካማችን መደምደሚያ፣ የድላችን መዳረሻ፣ በድል ላይ ቆመን ለሌላ የላቀ ድል የምንነሣበት ልዩ ዓመት መሆኑንም አስረድተዋል።

ሁላችንም በሩጫ ትግል ሊያልቅ ሲል እንደሚበረቱት፤ ሊጠናቀቅ ሲል እንደሚፈጥኑት ጀግኖች አትሌቶቻችን ካለፉት ዓመታት አስበልጠን እንትከል! እንበርታ! እንፍጠን! ሲሉም አሳስበዋል።