Search

ፈረንሳይ በምርምር ስም ወስዳቸው የቆዩትን የኢትዮጵያ የቅሪተ አካል ቅርሶች መለሰች

ሰኞ ሰኔ 08, 2018 60

ከኦሞ ሸለቆ ለሳይንሳዊ ምርምር ተወስደው በፈረንሳይ ሀገር ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት ተቀምጠው የነበሩ የቅሪተ አካል ቅርሶች ለኢትዮጵያ በይፋ ተመልሰዋል።

የተመለሱት ቅርሶች በጥንቃቄ የተያዙ ትላልቅ የቅሪተ አካል አጥንቶች፣ መንጋጋዎች፣ ጥርሶች እና የጥናት ናሙናዎችን ያካተቱ ናቸው።

እነዚህ ቅርሶች የሰው ልጅ ዘር አመጣጥ እና የዝግመተ ለውጥ ጥናት ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምትክ የሌላቸው ታሪካዊ እና ሳይንሳዊ ሀብቶች መሆናቸው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ፣ የፈረንሳይ መንግሥት የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርሶች ለመመለስ ያለውን ቁርጠኝነት በመግለጽ፣ የኦሞ ቅሪተ አካላት የጥናት ምዕራፍ ተጠናቅቆ ወደ እናት ሀገራቸው በመመለሳቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።

ይህም የሁለቱን ሀገራት የሳይንስ እና የባህል ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ኃላፊ ለፈረንሳይ መንግሥት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ የተረከቧቸው ቅርሶች ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ መሆኗን የሚያረጋግጡ ታሪካዊ ማስረጃዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቅርሶቹ በብሔራዊ ሙዚየም ተጠብቀው ለተመራማሪዎች እና ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚሆኑ እና በቀጣይም በውጭ የሚገኙ ቅርሶችን የማስመለስ ጥረት እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በቶክ ሮች