Search

አረንጓዴ ዐሻራ፤ ከችግኝ ተከላ ወደ አዲሱ የአኗኗር ዘይቤ

ሰኞ ሰኔ 08, 2018 55

በየዓመቱ በክረምት፣ ተፈጥሮ የዝናብ ካባን ለመጎናጸፍ ስትዘጋጅ፣ እኛም አንድ ትልቅ ብሔራዊ ቀጠሮ አለን። አረንጓዴ ዐሻራ!

ይህ መርሐ ግብር ዛሬ ላይ የዕፅዋት መትከያ ወቅታዊ ዘመቻ ብቻ መሆኑ አብቅቶለታል።

ይልቁንም ከዕለት ተለት ሕይወታችን፣ ከማሕበራዊ መስተጋብራችን እና ከማንነታችን ጋር የተሳሰረ፣ ትውልድ የሚቃኝበት አዲስና ውብ የኢትዮጵያውያን ባህል እየሆነ መጥቷል።

የዚህ አዲስ ባህል ትልቁ ማሳያ የሕብረተሰቡ የተሳትፎ መንፈስ ነው። ከሕፃናት እስከ አዛውንት፣ ከከተማ እስከ ገጠር ልዩነት ሳይገድበው መላው ሕዝብ የዚህ መርሐ ግብር ተሣታፊ ነው።

ትናንት በቡና ሥነ-ሥርዓትና በማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ይንጸባረቅ የነበረው አብሮነት፣ ዛሬ በችግኝ ተከላ ቦታዎች ላይ በአዲስ መልክ እየታየ ይገኛል።

አረንጓዴ ዐሻራ የጋራ ኃላፊነትን፣ አብሮ መሥራትንና ለሀገር ማሰብን በተግባር ያስተማረ፣ ማሕበራዊ ትስስራችንን ያጠናከረ አዲሱ ዘመናዊ መገለጫም ሆኗል።

ይህ ባህል በዜጎች የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ያመጣው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ቀደም ሲል አካባቢን መጠበቅና እንክብካቤ ማድረግ የጥቂት አካላት ሥራ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።

ዛሬ ግን “እኔ የምተክላት ችግኝ ለነገዋ አገር የምታበረክተው አስተዋፅኦ አላት” የሚል ጥልቅ የባለቤትነት ስሜትና ንቃተ-ሕሊና በሁሉም ዘንድ ሰርጿል።

ተክሎ ዝም ማለት ሳይሆን፣ ተንከባክቦ ማሳደግ፣ አረንጓዴ ቦታዎችን መውደድና መጠበቅ የዜግነት ኩራትና የሥልጣኔ መለኪያ እየሆነም መጥቷል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ባህልን ከቀዳሚው የተከላ ልምድ ለየት የሚያደርገው፣ ከውበትና ከጥላ ባለፈ ወደ ኢኮኖሚያዊ ትርጉም መሸጋገሩ ነው። አሁን የሚተከሉ ችግኞች የአየር ንብረትን ከመጠበቅ ባለፈ የጓሮ አትክልትና የፍራፍሬ ልማትን፣ አግሮ-ፎረስትሪንና የምግብ ዋስትናን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።

ይህም ማሕበረሰቡ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ምርታማነት የለወጠ፣ አረንጓዴ ልማትን ከኑሮ መሻሻል ጋር ያቆራኘ አርቆ አሳቢ ባህል እንዲገነባ አድርጎታል።

ለነገው ትውልድ የሚተርፈው ይህ አዲስ ባህል ለነገዎቹ ሕፃናትና ወጣቶች የሚተላለፍ ትልቅ የቅርስ አደራ ነው።

ዛሬ ትንሽ የችግኝ ዐሻራ የሚያሳርፉ ታዳጊዎች የነገዋን አረንጓዴና ለኑሮ ምቹ ኢትዮጵያን እየገነቡ መሆናቸውን በተግባር እየተማሩ ያድጋሉ።

አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያን ለዓለም የምናሳይበት፣ የአየር ንብረት ለውጥን በንቅናቄ የምንመክትበትና ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሰው አዲሱ የሕይወት ዘይቤያችን ነው።

በሔዋን ጌታቸው