Search

ኢራን እና አሜሪካ ጦርነት ለማቆም እና የሆርሙዝን ሰርጥን ዳግም ለመክፈት የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ላይ ደረሱ

ሰኞ ሰኔ 08, 2018 100

የአሜሪካ እና የኢራን ባለሥልጣናት ጦርነቱን ለማቆም እና የሆርሙዝ ሰርጥን ዳግም ለመክፈት የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

ስምምነቱ ገና በጅምር ደረጃ ላይ ቢሆንም፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ለሆነው እና የነዳጅ ገበያውን ላናጋው ግጭት መፍትሔ በማምጣት ረገድ ትልቅ እመርታ ነው ተብሏል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፣ "ከእስላማዊ የኢራን ሪፐብሊክ ጋር የተደረገው ስምምነት አሁን ተጠናቅቋል" ብለዋል።

ይህ መልዕክታቸው የወጣው አስታራቂ ሆና እየሠራች ያለችው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሻሪፍ ሁለቱ ሀገራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ካስታወቁ በኋላ ነው።

የመግባቢያ ሰነዱ ዓርብ ዕለት በስዊዘርላንድ በይፋ ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል።

ትክክለኛዎቹ የስምምነቱ ዝርዝሮች ወዲያውኑ እንዳልታወቁ ሬውተርስ በዘገባው ጠቅሷል።

ሻሪፍ በኤክስ ገጽ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፣ ስምምነቱ "በሊባኖስ ውስጥ ያለውን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች ወታደራዊ ዘመቻዎች በአስቸኳይ እና በዘላቂነት እንዲቆሙ" የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢራን ከፍተኛ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ሴክሬታሪያት ባወጣው መግለጫ፣ ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች ጦርነት እና ወታደራዊ ዘመቻዎች ከሰኞ ምሽት ጀምሮ በዘላቂነት እንደሚቆሙ አስታውቋል።

የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ እንዳሉት፣ በ60 ቀናት የተኩስ አቁም ጊዜ ውስጥ በኢራን ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ማንሣትን ጨምሮ ይበልጥ ሰፊ የሆነ ስምምነት ይደረጋሉ።

ሌላው አወዛጋቢ ጉዳይ የሆነው የኢራን የኑክሌር ፕሮግራም ዕጣ ፈንታ በእነዚሁ ቀጣይ ድርድሮች ላይ እንደሚነሣ ምንጮች ቀደም ሲል ገልጸዋል።

በአሜሪካ እና በኢራን ንግግሮች ውስጥ ተሳታፊ እንዳልነበረች ለገለጸችው እስራኤል፣ ስለ ስምምነቱ መታወጅ ወዲያውኑ የሰጠችው ምላሽ የለም።

ትራምፕ እንዳሉት፣ ኢራን ለወራት ዘግታው የቆየችው እና ለዓለም አቀፍ የነዳጅ እና ጋዝ አቅርቦት ዋና የትራንስፖርት መስመር የሆነው የሆርሙዝ ሰርጥ ዓርብ ዕለት ይከፈታል፤ አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን እገዳ እንዲያበቃ ትዕዛዝ መስጠታቸውንም ገልጸዋል።

"የዓለም መርከቦች፣ ሞተሮቻችሁን አስነሱ፤ ነዳጅ ይፍሰስ!" ብለዋል ትራምፕ በመልዕክታቸው።

በዚሁ የስምምነት ዜና ምክንያት የነዳጅ ዋጋ የቀነሰ ሲሆን ሰኞ ማለዳ ላይ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በ4% ሲቀንስ፣ በእስያ የአክሲዮን ገበያዎች ላይ ግን ጭማሪ ታይቷል።

በመካከለኛው ምስራቅ ውጭ ያሉ እና ግጭቱን በስጋት ሲከታተሉ የነበሩ መሪዎች፣ የስምምነቱን መታወጅ በደስታ ተቀብለውታል።

ብሪታንያ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ ኢራን የኑክሌር ፕሮግራሟን ለመገደብ ለምትወስዳቸው ግልጽ እና ሊረጋገጡ የሚችሉ እርምጃዎች ምላሽ የተጣለባትን ማዕቀብ ለማንሣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከስምምነቱ መታወጅ በፊት አንድ ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣን እንደገለጹት፣ በረቂቅ ስምምነቱ መሠረት አሜሪካ የታገደውን 25 ቢሊዮን ዶላር የኢራን ሀብት ለመልቀቅ ትስማማለች።

የትራምፕ አስተዳደር ከዚህ ቀደም የትኛውም የኢራን ገንዘብ የሚለቀቀው ኢራን በሰላም ስምምነቱ መሰረት የተወሰኑ ሁኔታዎችን ስታሟላ ብቻ ነው ብሎ ነበር።

በዮናስ በድሉ