Search

ሰው ሠራሽ አስተውሎ (AI) አዲሱ የዓለማችን የታሪክ መታጠፊያ እና የኢትዮጵያችን ብሩህ ተስፋ

እሑድ ሐምሌ 19, 2018 34

ሰው ሠራሽ አስተውሎ (AI) ለዛሬው የዓለማችን የቴክኖሎጂ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የፈጠራ እና የተወዳዳሪነት ዋና መሠረት በመሆን የነገውን ኢ-ተገማች ዓለም የሚቀርጽ የኃይል ሚዛን እየሆነ ይገኛል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት አፍሪካ ተገቢውን የዲጂታል መሠረተ ልማት፣ የሰው ኃይል ክህሎት እና የፖሊሲ ድጋፍ ካጠናከረች ኤአይ (AI) የአህጉሪቱን አጠቃላይ ምርት (GDP) በ4 በመቶ ሊያሳድግ እንደሚችል አመላክቷል።

በሌላ በኩል የአፍሪካ ልማት ባንክ (AfDB) በአውሮፓውያኑ 2035 ኤአይ ለአፍሪካ እስከ 1 ትሪሊየን ዶላር የሚደርስ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ገቢ ሊፈጥር እንደሚችል ይተነብያል።

እነዚህ ቁጥሮች ትንበያዎች ብቻ ሳይሆኑ እንደ አህጉር እና እንደ ሀገር ልንከተለው የሚገባንን ወሳኝ አቅጣጫ የሚያሳዩ የኢኮኖሚ መነቃቃት ጥሪዎች ናቸው።

ትላንት በሳይንስ ሙዚየም የተመረቁት የኤአይ ጀማሪ (Startup) ድርጅቶች እና የፈጠራ ሥራዎች ይህ የወደፊት ራዕይ በኢትዮጵያችን ውስጥ በእውነተኛ መሠረት ላይ መገንባት መጀመሩን ያረጋግጣሉ።

ወጣቶቻችን በቴክኖሎጂ ፈጠራ እያሳዩት ያለው ድንቅ አቅም፣ ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እና ተጠቃሽ ብቻ ሳትሆን አፍላቂ፣ ፈጣሪ እና ላኪ ሀገር መሆን እንደምትችል ግልጽ ማረጋገጫ ነው።

የሀገራችን ፍኖተ ካርታ የሆነው የ"Digital Ethiopia 2030" ስትራቴጂም ይህንን ራዕይ በተግባር ለማሳካት የተዘጋጀ ወቅታዊ እና ስልታዊ መላ ነው።

የዲጂታል መሠረተ ልማትን ማጎልበት፣ የወጣቶችን የቴክኖሎጂ ክህሎት ማሳደግ፣ የምርምርና የፈጠራ ምኅዳርን ማጠናከር እና ለጀማሪ የፈጠራ ድርጅቶች (Startups) ምቹ ሥነ-ምኅዳር መፍጠር የዚህ ታሪካዊ ጉዞ ዋና ምሰሶዎች ናቸው።

በእርግጥም ኤአይ በግብርና ምርታማነት፣ በኢንዱስትሪ መዋቅራዊ ሽግግር፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ እና በንግድ ውድድር ላይ አዲስ ብርሃን የሚፈነጥቅ የልማት እና የሉዓላዊነት መሣሪያ ነው።

በታሪክ አጋጣሚዎች ቀደም ሲል የነበሩትን የኢንዱስትሪ አብዮቶች (1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ) ተረድተን በወቅቱ ባለመቀላቀላችን፣ ሀገራት በኢንዱስትሪ እና በኢኮኖሚ ዕድገታቸው 1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ዓለም ተብለው ሲከፈሉ እኛ ከኋላ ቀሪዎቹ ተራ ውስጥ እንድንመደብ አድርጎናል።

የአሁኑ የኢትዮጵያ ኤአይ አብዮት ይህንን የቆየ ክፍፍል ሙሉ በሙሉ የሚሽር ነው። ከእንግዲህ 1ኛ እና 3ኛ ዓለም የሚለው ስያሜ የሚዘልቅ አይሆንም። በምትኩ ዓለም በሁለት አዲስ ዋልታዎች ልትከፈል ትችላለች።

አንደኛው በፈጣኑ የኤአይ የቴክኖሎጂ ባቡር ላይ ተሳፍረው የብልጽግና እና የኃይል ማዕከል የሚሆኑ ሀገራት ሲሆኑ፣ ሁለተኛው ደግሞ ከባቡሩ ወደኋላ ቀርተው ከዓለም አቀፍ ዕድገት ጋር የሚያገናኛቸው ድልድይ ተሰብሮ "የወዲያኛው ዓለም" ነዋሪዎች የሚሆኑ ናቸው።

ይህ የኤአይ ዘመን በፊታችን እና በእጃችን ላይ ያለ፣ ካወቅንበት እና ከተጠቀምንበት ታላቅ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ዕድገት መታጠፊያ አጋጣሚ፤ ችላ ብለን ካለፍነው ደግሞ የዘላለም ተረሺነት ፈተና ነው።

በቴክኖሎጂ፣ በዕውቀትና በወጣቶቻችን ፈጠራ ላይ የምናደርገው ኢንቨስትመንት የአሁኑ ምርጫችን ብቻ ሳይሆን የነገዋን ኢትዮጵያ ህልውና እና የኢኮኖሚ የበላይነት የመወሰን ጉዳይ ነው።

የሀገራችን መፍትሔ ኢትዮጵያን በኤአይ ቴክኖሎጂ ይበልጥ ማላቅ እና የትውልዱን አቅም ወደዚህ ፈጣን ባቡር ማሸጋገር ነው። ዛሬ በዘርፉ ተሰማርተው የምናያቸው ወጣቶች ይህንን አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችሉ ትልልቅ የነገ ተስፋዎቻችን ናቸው።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: