Search

የኢትዮጵያ ኮደሮች ዲጂታል ጉዞ፡- ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወደ ፈጣሪነት

ቅዳሜ ሐምሌ 25, 2018 54

በዓለም አቀፍ ደረጃ ዲጂታል ኢኮኖሚ የሀገራትን ዕድገት በሚወስንበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋን በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ ላይ ለመመስረት ደፋር እና ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች።

ከእነዚህም መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አነሳሽነት ይፋ የተደረገው5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ኮደርስሥልጠና ዋነኛው እና ትልቁ ፕሮጀክት ነው።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን ሊሆን የሚችለው በብቁ እና በሠለጠነ የሰው ኃይል ነው። ‘5 ሚሊየን ኮደርስፕሮግራሞች በዋናነት የሚያተኩረውም ዌብሳይት ዲቨሎፕመንት፣ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስና ዳታ ሳይንስ፣ አንድሮይድ አፕ ዲቨሎፕመንት እና ሳይበር ሴኪዩሪቲ ላይ ነው።

መንግሥት ወጣቶች በእነዚህ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መስኮች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሥልጠናዎችን በነጻ እንዲወስዱ ማድረጉ ሀገራችን በቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚያጋጥማትን የክህሎት ክፍተት በፍጥነት እንድትሞላ ያስችላታል።

ለሚሊዮን ወጣት የሥራ ዕድል መፍጠር ለኢትዮጵያ ወሳኝ ጉዳይ ሲሆን፣ ይህ ኢኒሼቲቭ ወጣቶች በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነው እንዲሠሩ ዕድል ይከፍትላቸዋል።

ወጣቶች በዓለም አቀፍ የፍሪላንስ ሥራ ዕድል መድረኮች ላይ በመሰማራት የውጭ ምንዛሪን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያስገቡ ያግዛል። እንዲሁም በሥልጠናው ያገኙትን የኮዲንግ እና የችግር ፈቺነት ክህሎት በመጠቀም የሀገር በቀል ችግሮችን የሚፈቱ የቴክኖሎጂ ስታርታፖችን (Tech Startups) እንዲመሰርቱ መንገድ ይጠርግላቸዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት፣ አገልግሎቶቿን ወደ ዲጂታል የመቀየር (Digital Transformation) ጉዞ ላይ ትገኛለች። እንደ ፋይናንስ፣ እርሻ፣ ጤና እና ትምህርት የመሳሰሉት ዋና ዋና ዘርፎች የሶፍትዌር ውጤቶችን ይፈልጋሉ።

በዚህ ፕሮግራም የሚወጡ አዳዲስ ኮደሮች ለሀገራችን የዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታ፣ ለኢ-ኮመርስ (e-Commerce) እና ለመንግሥታዊ አሠራሮች ማዘመን (e-Government) እንደ ትልቅ ሞተር ሆነው ያገለግላሉ።

ሥልጠናውን ልዩ የሚያደርገውም በከተማ ለሚኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ በየክልሉ ለሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወጣቶች እና ፍላጎት ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ክፍት መሆኑ ነው።

ኢኒሼቲቩ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግም ሰፊ ዕድል መፍጠር ችሏል። ወጣቶች ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት አልፈው የቴክኖሎጂ ፈጣሪ እንዲሆኑ አስተሳሰባቸውን ቀይሮታል፤ ይህም የሀገራችንን ዲጂታል ብቃት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል።

5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ኮደርስኢኒሼቲቭ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ዲጂታል መዋቅር የሚገነባ ትልቅ ስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንት ነው። ይህ ፕሮግራም ወጣቶችን በዘመናዊ ክህሎት በማስታጠቅ፣ የኢኮኖሚ ዕድሎችን በመፍጠር እና ሀገራችን በምስራቅ አፍሪካ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ማዕከል በማድረግ ረገድ የሚጫወተው አስተዋጽዖም የማይተካ ነው።

በቀጣይም የሠለጠኑትን ወጣቶች ከሀገር ውስጥ እና ከዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ ጋር የሚያገናኙ መድረኮች እና አሠራሮች ተጠናክረው ከቀጠሉ፣ የኢትዮጵያ የዲጂታል ጉዞ የተፋጠነና የተሳካ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።

በአድማሱ አራጋው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: