የመካከለኛው ምሥራቅ ሰማይ በጦርነት ጭስ ተውጦ፣ የዓለም የጂኦፖለቲካ ምህዋር ሊመጣ ከሚችለው የከፋ አደጋ አንፃር ትንፋሹን ውጧል።
ባለፈው ወር በፓኪስታን አደራዳሪነት የተደረሰው የጋራ መግባቢያ ስምምነት እንደ ሐር እየተነጠለ፣ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የነበረው ቀዝቃዛ ጦርነት አሁን ላይ ወደ አደገኛ እና ቀጥተኛ ወታደራዊ ፍጥጫ ተሸጋግሯል።
የኒውክሌር ተቋማት የሚሳኤል ኢላማ ሲሆኑ፣ የዓለም የነዳጅ የደም ዝውውር የሆኑት የባህር ሰርጦች መዘጋታቸው፣ የሰው ልጅ ወደማይታይ የጸጥታ ቀውስ ውስጥ እየገባ መሆኑን በግልጽ እየተመሰከረ ይገኛል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በዮርዳኖስ ወታደራዊ የጦር ሰፈር ላይ በተሰነዘረ የድሮን ጥቃት የወታደሮቹን መገደል ሲያበስር፣ ዋሽንግተን የወሰደችው አጸፋዊ እርምጃ የሁኔታውን አሳሳቢነት ወደላቀ ደረጃ ከፍ አድርጎታል።
በደቡባዊና ደቡብ ምዕራብ ኢራን በሚገኘው የዳርክሆቨይን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታ ቦታ ላይ ያነጣጠረው የሚሳኤል ጥቃት፣ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ያነጋገረ አወዛጋቢ ክስተት ሆኗል።
ፔንታገን ጥቃቱን በቀጥታ ከማረጋገጥ ቢቆጠብም፣ የኢራን የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ግን ይህንን ድርጊት የሳይንስ ዕድገት ለማጥፋት የታለመ የሽብር ጥቃት ሲል በጽኑ አውግዞታል።
በአንጻሩ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ኃይል ‘ናስር-2’ እና መደበኛው ጦር ‘ሳዕቃ’ በኩዌት፣ ባህሬን እና ዮርዳኖስ በሚገኙ የአሜሪካ ቁልፍ የጦር ሰፈሮች ላይ የሰነዘሩት አጸፋዊ የኃይል እርምጃ በአካባቢው ሌላ ትኩሳትን ፈጥሯል።
የዋሽንግተን ፖስት የምርመራ ሪፖርት በሳተላይት ምስሎች እንዳረጋገጠው፣ በቀጣናው በሚገኙ 15 የአሜሪካ ወታደራዊ ይዞታዎች ውስጥ 228 መዋቅሮች በከፊልም ሆነ በሙሉ መውደማቸው ውጥረቱ የፈጠረውን ከፍተኛ ውድመት ያሳያል።
የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩላቸው፣ በኒውክሌር መሠረተ-ልማቶች ላይ የሚደረግ ወታደራዊ ጥቃት በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለ መሆኑን በማስታወስ ሁለቱም ወገኖች በአስቸኳይ ራስን የመግታት እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል።
በፖለቲካው መድረክ ያለው የቃላት ጦርነትም ከወታደራዊው እርምጃ ያነሰ አይደለም። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር ታጣቂ እንድትሆን ፈጽሞ እንደማይፈቅዱ በድጋሚ አሳስበዋል።
የኢራን መንፈሣዊ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ እና የፓርላማው አፈ-ጉባኤ መሀመድ ባቄር ቃሊባፍ ደግሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ፊርማ ፍጹም ዋጋ ቢስ መሆኑን በመግለጽ ሕዝባቸው ወታደራዊ ዝግጁነት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
አሜሪካ በኢራን ላይ የባሕር እገዳ ለመጣል ስትሞክር፣ ቴህራን በበኩሏ የዓለምን የነዳጅ የደም ሥር የሆነውን የሆርሙዝ ሰርጥ ሙሉ በሙሉ መዝጋቷን አውጃለች።
ይህንን ተከትሎ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በአንድ ጀምበር ያሳየው ጭማሪ፣ ቀውሱ ከቀጣናዊ ጦርነት አልፎ በኤዥያ እና በአውሮፓ አገራት ላይ ከባድ የነዳጅ እጥረትና የዋጋ ግሽበት ሊያስከትል እንደሚችል እያሳየ ነው።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለቱ ኃይላት ወደ የማይመለስበት ጦርነት ከመግባታቸው በፊት አፋጣኝ የዲፕሎማሲ እጅ በመዘርጋት ሰላም እንዲያወርዱ ፍላጎቱ ሆኗል።
በአዝመራው ሞሴ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: