በቅርቡ በሺንጂያንግ ግዛት በተደረገ ጉዞ፣ በቅርብ ጊዜ ክፍት በረሃ በነበሩ አካባቢዎች አዳዲስ የተተከሉ እና ገና ያልጎመሩ ዛፎች አውራ ጎዳናዎችን አጅበው መመልከት የተለመደ ትዕይንት ሆኗል። ከቱርፓን እስከ ኡሩምኪ ዳርቻዎች የሚታየው ይሄው ተመሳሳይ ገጽታ፣ ይህ ምንድን ነው? እና ምን ያህል ጊዜ ፈጅቷል? የሚል ጥያቄን በውስጥ ያጭራል። ምላሹ አሁን በመንገዱ ላይ ከሚያልፉት አብዛኛዎቹ ሰዎች ዕድሜ የሚበልጥ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑ ነው።
የፕሮጀክቱ ዋና ሀሳብ ቀላል ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ ግን አሥርተ ዓመታትን የወሰደ ነው። በሰዎች የተተከሉት የዛፍ መስመሮች ንፋስን በመግታት የጎቢ በረሃ መስፋፋትን የሚከላከሉ ሲሆን፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብም የጣውላ ምንጭ ሆነው ያገለግላሉ።
በ1978 የተጀመረው ይህ ፕሮግራም እስከ 2050 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ሲሆን፣ ሲጠናቀቅ ወደ 3000 ማይልስ ርዝመት እና 88 ሚሊዮን ኤከር የደን ሽፋን ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። ቻይና በዓለም ላይ ካሉ ሀገራት በበረሃማነት ስድስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ ይህንኑ አስከፊ የበረሃ መስፋፋት ለመቀልበስ "ታላቁ አረንጓዴ ግንብ" እየተገነባ ይገኛል።
ከ1978 ዓ.ም ጀምሮ ሠራተኞች የጎቢን እና የታክላማካንን በረሃዎች ወደፊት መገስገስ ለመግታት 66 ቢሊዮን የሚገመቱ ዛፎችን ተክለዋል። በ2024 የፊንላንድን የሚያህል ስፋት ያለውን የታክላማካን በረሃ የሚከበው የ3044 ኪሎ ሜትር አረንጓዴ ቀበቶ የመጨረሻው ክፍተት ተዘግቷል።
የቻይና የሳይንስ አካዳሚ ተመራማሪ የሆኑት ዡ ጂያኦጁን እንዳስገነዘቡት፣ ከ2000 ወዲህ የቻይና በረሃማ መሬት በ10 በመቶ ሲቀንስ፣ እጅግ የከፋ በረሃማነት የታየባቸው አካባቢዎች ደግሞ ከ40 በመቶ በላይ ቀንሰዋል።
በፕሮግራሙ በተሸፈኑ አካባቢዎች የነበረው የደን ሽፋን በ1978 ከነበረው 5 በመቶ በ2022 ወደ 14 በመቶ ማደጉ የፕሮጀክቱን ስኬት በተጨባጭ ያሳያል። ዛፎች በፍጥነት እያደጉ በመሆናቸው፣ በታክላማካን ዙሪያ ያለው አረንጓዴ ቀበቶ በረሃው ከሚለቀው በላይ ካርቦን በመምጠጥ ላይ ይገኛል።
ታሪኩን ይበልጥ ሳቢ የሚያደርገው ዛፎቹ ከጸደቁ በኋላ የተፈጠረው ክስተት ነው። በኩቡኪ በረሃ፣ ሠራተኞች ዛፍ በመትከል ብቻ አላቆሙም፤ በተረጋጋው አሸዋ ላይ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎችን ገንብተዋል። እነዚህ ማመንጫዎች ለዋናው መረብ ኃይል ከማመንጨት ባሻገር፣ ጥላ በመፍጠር የውሃ ትነትን ስለሚቀንሱ ከስራቸው ቁጥቋጦዎችና ሳሮች እንዲበቅሉ አስችለዋል።
የኩቡኪ ፕሮጀክት ከ500 ቢሊዮን ዩዋን በላይ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያስገኘ ሲሆን፣ ከ100 ሺህ በላይ የአካባቢውን ነዋሪዎች ከድህነት በማውጣት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድሎችን ፈጥሯል።
አሁን ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች የፀሐይ ፓነሎቹን በመንከባከብ፣ ከሥራቸው ሰብሎችን በማምረት እና በአዲሱ የሳር ምድር ላይ እንስሳትን በማርባት ላይ ሲሆኑ፣ ፀረ-በረሃማነት ትግሉ እና የገቢ ምንጭ መፍጠር አብረው ሊሄዱ እንደሚችሉ በተግባር አሳይተዋል።
የቻይና አካሄድ ንፋስን ለመስበር እና ችግኞች ፀድቀው ስር እንዲሰድዱ የደረቁ ዕፅዋትን በቼዝ ሰሌዳ ቅርጽ በማዘጋጀት ላይ የተመሰረተ ቀላል ግን እጅግ ውጤታማ ዘዴ ነው። ከ2018 ጀምሮ ቻይናውያን ተመራማሪዎችና መሐንዲሶች በሳህል ቀጠና መሬትን መልሶ ለማልማት በ2007 ከተጀመረው የአፍሪካ ታላቁ አረንጓዴ ግንብ ተነሳሽነት አባል ከሆኑት ኢትዮጵያ፣ ሞሪታንያ እና ናይጄሪያ ጋር በመተባበር ላይ ይገኛሉ።
ይህ ትብብር የሳተላይት ክትትልን እና የርቀት ዳሳሾችን ጭምር ያካተተ ሲሆን፣ አፍሪካውያን አጋሮች የመሬት መራቆትን ቻይና የራሷን የከለላ ቀበቶ በምትከታተልበት መንገድ በቅጽበት መከታተል እንዲችሉ አድርጓል።
ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ገና አላለቀም፤ ቻይና በሚቀጥሉት 25 ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ 34 ቢሊዮን ዛፎችን ለመትከል አቅዳለች። ይህ ማለት በ1980ዎቹ ፕሮጀክቱን የጀመሩት ሠራተኞች አሁን ልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው በዚያው በረሃ ላይ ሥራውን ሲያስቀጥሉ እያዩ ነው።
እንደ ቻይና ፎከስ ዘገባ ተፈጥሮን የመታደግ ሥራ ቀስ ብሎ የሚጓዝ፣ ተደጋጋሚ እና አሥርተ ዓመታትን የሚጠይቅ ቢሆንም፣ በረሃው መስፋፋቱን እስኪያቆም ድረስ በየጊዜው በአሸዋ ላይ አንድ ትንሽ ጉድጓድ በመቆፈር የሚገነባ ዘላቂ የድል ጉዞ ነው።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: