Search

800 ሚሊዮን ሕይወት በአንድ ጀምበር! - ኢትዮጵያ ለዓለም የምታበረክተው ተጨማሪ ስጦታ!

እሑድ ሐምሌ 26, 2018 58

ነገ (ሐምሌ 27 ቀን 2018 .) የኢትዮጵያ ፀሐይ ስትወጣ፣ ኢትዮጵያውያን ሌላ አዲስ ታሪክ ይጽፋሉ።

እንደ ሀገር እና እንደ ሕዝብ አንድ ላይ ቆመን በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የዓለምን ክብረ ወሰን በድጋሚ ለማደስ እና የምድር ሳንባ የበለጠ ንፁህ አየር እንዲተነፍስ ለማድረግ ተዘጋጅተናል።

ይህ ክስተት ከቁጥር ባለፈ፣ የኢትዮጵያውያን ተፈጥሮን የማከም፣ የመጠበቅ እና ለቀጣዩ ትውልድ አረንጓዴ እና ለምለም ሀገር የማስረከብ ጽኑ ቃል ኪዳን ማረጋገጫ ነው።

ወደ ነገው ታላቅ የታሪክ መድረክ ከመሸጋገራችን በፊት፣ ዛሬ ላይ ሆነን ትናንትን መቃኘት ተገቢ ነው።

2011 . በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አነሣሽነት "የአረንጓዴ ዐሻራ" መርሐ ግብር ሲጀመር፣ ዓላማው የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነበር።

በወቅቱ በአንድ ጀምበር 350 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ዓለምን ጉድ ያሰኘንበት እና ጉዟችንን በይፋ የጀመርንበት ዓመት ነበር።

2015 . ደግሞ ይህንኑ የራሳችንን ሪከርድ በማሻሻል በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ተክለናል።

2017 . በአንድ ጀምበር 714 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በላይ ተክለን የማይቻል የሚመስለውን ታሪክ ጽፈን ለዓለም አሳይተናል።

በነገው ዕለት ደግሞ በተደመረ አቅም ወጥተን፤ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ራዕይ ሰንቀናል። ይህ ራዕይ የሀገራችንን የግብርና ባለሙያዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ ወጣቶችን፣ እናቶች እና አባቶችን በአንድ ልብ ያስተሣሠረ ነው።

ለዚህ ዝግጅት የግብርና ሚኒስቴር ባለሙያዎች የችግኞቹን ዓይነት በጥንቃቄ መርጠዋል። በዚሁ መሠረት የተዘጋጁት ችግኞች መካከል፦

የፍራፍሬ ችግኞች (አግሮ-ፎረስትሪ) ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ማንጎ እና አፕልን የመሳሰሉ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ እና ለአርሶ አደሩ የኢኮኖሚ አቅም የሚፈጥሩ።

የሀገር በቀል ዛፎች፦ እንደ ኮሶ፣ ዋንዛ፣ ጽድ እና ዝግባ ያሉ ሥነ-ምኅዳራችንን የሚጠብቁ።

የእንስሳት መኖ እና የጥላ ዛፎች፦ የተራቆቱ መሬቶችን መልሰው የሚያለመልሙ እና አፈርን ከእጥበት የሚከላከሉ ይገኙባቸዋል።

በነገው ዕለት ማለዳ፣ ከራስ ዳሸን ተራሮች እስከ ኦጋዴን በረሃዎች፣ ከሶፍ ዑመር ዋሻዎች እስከ ዳሎል አቅራቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያን በያሉበት ቦታ ላይ በገቢር አስደናቂ ታሪክ ይጽፋሉ።

800 ሚሊዮን ችግኞች ማለት 800 ሚሊዮን አዳዲስ ሕይወቶች ማለት ነው። ይህ ትውልድ የጦርነት እና የድህነትን ታሪክ ወደ ጎን ትቶ፣ የልምላሜ እና የብልጽግና ታሪክ እየጻፈ መሆኑን ለዓለም የምናሳይበት ታላቅ አውድማ ነው።

በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የዓለምን የአየር ንብረት ትግል ወደ አዲስ ከፍታ የሚያሸጋግር ደማቅ ዐሻራ ልናሳርፍ የሰዓታት ዕድሜ ብቻ ቀርቶናል።

ነገ እንገናኝ! ዐሻራችንን እናኑር፤ በጋራ ተስፋን እንትከል!

በዮናስ በድሉ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: