የብሪክስ አባል አገራት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ያላቸውን ሚና ይበልጥ ለማሳደግና የኢኮኖሚ ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ የወርቅ ክምችታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደጉ ይገኛሉ።
ምንም እንኳን አገራቱ በይፋ የያዙት የወርቅ ክምችት ከዓለም አቀፉ ድርሻ 20 በመቶ ቢሆንም፣ ከአጋር አገራት ጋር በመቀናጀት አሁን ላይ የዓለምን ግማሽ ያህል የወርቅ ምርት መቆጣጠር መቻላቸው ተመላክቷል።
በዚህ ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ሩሲያና ቻይና በከፍተኛ ምርት ግንባር ቀደሙን ስፍራ የያዙ ሲሆን፣ ብራዚልም በተመሳሳይ በቅርቡ ከፍተኛ የወርቅ ግዢ በመፈጸም የክምችት መጠኗን አሳድጋለች።
የፋይናንስ ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት፣ የብሪክስ አገራት ወርቅን በብዛት በማምረትና ለውጭ ገበያ ባለመሸጥ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ገበያ የሚገኘውን ድርሻ በመሰብሰብ የራሳቸውን የፋይናንስ መተማመኛ መልህቅ እየገነቡ ነው።
አገራቱ ለወርቅ ክምችት ልዩ ትኩረት የሰጡት የኢኮኖሚ ነጻነትን ለማወጅና የንግድ ልውውጦችን አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለመምራት በማለም ነው።
በአሁኑ ወቅት ከብሪክስ አገራት የንግድ ልውውጥ ውስጥ ሲሶ ያህሉ በአባል አገራቱ ብሔራዊ ገንዘቦች እየተከናወነ ይገኛል። በተለይም "ዩኒት" የተሰኘውና በከፊል በወርቅ የሚደገፈው አዲሱ የክፍያ ሥርዓት በሙከራ ላይ መሆኑ፣ የዓለም የፋይናንስ ሥርዓት ወደ ብዙ አማራጮች እንዲሸጋገር ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ነው።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ይህ የብሪክስ የወርቅ ስትራቴጂ ለአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትና አስተማማኝ የንግድ ሥርዓት ለመዘርጋት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
አባል አገራቱ በወርቅ የተደገፈ የልውውጥ ሥርዓት ማጠናከራቸው፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የተፈጥሮ ሀብት ያላቸው አገራት በዓለም አቀፍ ገበያ ያላቸውን የመደራደር አቅም እንደሚያሳድገውም ይጠበቃል።
በሰለሞን ገዳ
#EthiopianBroadcastingCorporation #Ebcdotstream #Ethiopia #BRICS #GoldStrategy #UnitCurrency