ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ያላት አቋም በታሪክ ማኅደር ውስጥ በወርቅ ቀለም የተጻፈ፣ በጽናትና በቆራጥነት የታጀበ የነፃነት ተጋድሎ ነው። ይህ በቅኝ አገዛዝ ዘመን ያልበገረው የጥቁር ሕዝቦች ኩራት፣ "ኢትዮጵያ ልቧን ለአፍሪካ ወንድሞቿ ትከፍታለች" የሚለውን ጥልቅ እውነታ በተግባር ሲያረጋግጥ ኖሯል። ይህም ኢትዮጵያ የአህጉሪቱ እናት፣ የአንድነቷ መሐንዲስ እና የነፃነቷ ዘብ ሆና የቆመችው ድርሳናትን በማገላበጥ የታሪክ ማስረጃዎች ጭምር በማጣቀስ የሚገለጥ እውነት ነው።
ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ድረስ ያሉ የኢትዮጵያ መሪዎች በአንድ ታላቅ ራዕይ ይተሳሰራሉ፤ እርሱም "አፍሪካ በራሷ እግር መቆም አለባት" የሚለው ጽኑ መርህ ነው።
በአውሮፓውያኑ 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ ሲመሰረት፣ ኢትዮጵያ አህጉሪቱን በአንድ ጥላ ሥር ለማሰባሰብ ያደረገችው ተጋድሎ ለዛሬው የአፍሪካ ሕብረት መሠረት ጥሏል። በወቅቱ አፍሪካ በሞንሮቪያ እና በካዛብላንካ ቡድኖች ተከፋፍላ በነበረችበት ወቅት፣ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ እንደ አርቆ አሳቢ መሪ ሁለቱንም ወገኖች አዲስ አበባ ላይ በማስታረቅ ታሪካዊ አንድነትን ፈጥረዋል። ጃንሆይ ያኔ ያስተላለፉት "አፍሪካ ዛሬ አንድ ካልሆነች ነገ ተከፋፍላ ትቀራለች" የሚለው ማስጠንቀቂያ፣ ዛሬም ድረስ የአህጉሪቱ መመሪያ ሆኖ ያገለግላል።
ይህ የጽናት ጉዞ በንግግር ብቻ የተገደበ አልነበረም። ኢትዮጵያ ለነፃነት የታገሉ የአፍሪካ የቁርጥ ቀን ልጆች አስተማማኝ መጠጊያ ነበረች። ወጣቱ ኔልሰን ማንዴላ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድን ሥርዓት ለመጣል በድብቅ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በኮልፌ ፖሊስ ማሠልጠኛ ወታደራዊ ስልጠና የወሰደውና የኢትዮጵያን ፓስፖርት ይዞ ዓለምን የዞረው በመሪዎቿ ይሁኝታ ነበር። ማንዴላ "ረጅሙ የነፃነት ጉዞ" በተሰኘው መጽሐፋቸውም እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ለእርሳቸው የነፃነትና የጥቁር ሕዝብ ኩራት ተምሳሌት ነበረች።
ዛሬም ይህ የታሪክ ሰንሰለት ሳይበጠስ ወደ አዲሱ ትውልድ ተሸጋግሯል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ፣ የኢትዮጵያን የቆየ የፓን-አፍሪካኒዝም ታሪክ በአዲስ መንፈስና በዘመናዊ እይታ እያቀነቀኑት ይገኛሉ።
የእሳቸው አቋም "አፍሪካዊ መፍትሔ ለአፍሪካዊ ችግሮች" ከሚለው መርህ አልፎ፣ አህጉሪቱን በዓለም መድረክ ላይ ተደማጭነት ያላት ኃያል ተዋናይ ለማድረግ ያለመ ነው። አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ወንበርና ተገቢ ውክልና እንዲኖራት በጽናት የሚታገሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "አንድ ቢሊዮን ሕዝብ ያላት አህጉር ድምፅ አልባ መሆን የለባትም" የሚል ጽኑ አቋም አላቸው።
ከዲፕሎማሲው ባለፈ፣ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመከላከል የምታደርገው ጥረት፣ ለጎረቤቶቿ የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይልና የምትገነባቸው ድንበር ተሻጋሪ መሠረተ ልማቶች የአህጉሪቱን የ"አጀንዳ 2063" ራዕይ በተግባር እየተረጎሙት ይገኛሉ።
አዲስ አበባን የአፍሪካ የለውጥ ሞተር የማድረግ ፍላጎት፣ ታሪካዊ ግዴታን ከዘመናዊ ብልጽግና ጋር የማጣመር ጥበብ ውጤት ነው።
አፍሪካ የግጭትና የድህነት ምድር መሆኗ አብቅቶ፣ የፈጠራና የብልጽግና ማዕከል የምትሆንበት ዘመን ግን ሩቅ እንደማይሆን የኢትዮጵያ መሪዎች ቁርጠኝነት ከፍተኛ ስለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም ምክንያቱም የኢትዮጵያ መሪዎች በአህጉሪቱ ጉዳይ ላይ ያላቸው ጽናት ከሀገራዊ ጥቅም በላይ ለሆነው "አፍሪካዊ ኩራት" የሚከፈል ዋጋ ስለሆነ የሚለው ትክክለኛው መልስ ነው።
ይህ ተከታታይነት ያለው ጽናት ነው ዛሬም ድረስ አዲስ አበባን የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ዋና መዲና እና የአንድነት መንፈስ ምንጭ አድርጎ ያቆያት።
በቶማስ ሃይሉ
#EthiopianBroadcastingCorporation #Ethiopia #AfricanUnion #AUSummit2026 #Agenda2063 #AddisAbaba #Diplomacy #Africa