Search

ፊፋ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ የፕላስቲክ ቁሳቁሶችን ወደ ስታዲየም ይዞ መግባት ከለከለ

ሓሙስ ግንቦት 27, 2018 90

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) 2026 የዓለም ዋንጫ ተመልካቾች በድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ የፕላስቲክ ቁሳቁሶችን ወደ ስታዲየም ይዘው እንዳይገቡ የሚከለክል አዲስ መመሪያ ማውጣቱን አስታውቋል።

ይህ በመጨረሻው ሰዓት ላይ በስታዲየም የሥነ-ምግባር ደንብ ላይ የተደረገውና ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ተፈጻሚ መሆን የጀመረው ማሻሻያ፥ ከዚህ ቀደም ባዶና ግልጽ የሆኑ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ይዞ ለመግባት ይፈቀድ የነበረውን አሠራር ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር ነው።

አዲሱ እገዳ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ብቻ ሳይሆን ኩባያዎችን፣ ከጠርሙስም ይሁን ከሸክላ የተሰሩ መያዣዎችን እና በቆርቆሮ የታሸጉ መጠጦችን የሚያካትት ሲሆን፥ ፊፋ ለዚህ እርምጃ ዋነኛ ምክንያት አድርጎ የጠቀሰው የተሳታፊዎችን ደህንነት ማስጠበቅን ነው።

እነዚህ ቁሳቁሶች በጨዋታ መሃል ስሜታዊ በሆኑ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ወይም ወደ ሌላ ተመልካች ሊወረወሩና ጉዳት ሊያደርሱ ስለሚችሉ፣ አደጋውን አስቀድሞ ለመከላከል ውሳኔው አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ፊፋ ገልጿ።

እንዲያውም ከዚህ ቀደም በበርካታ ስታዲየሞች የውጭ ጠርሙሶችን ይዞ መግባት በደህንነት ምክንያት የተከለከለ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ፊፋ ይህንን አሠራር በሁሉም የዓለም ዋንጫ ስታዲየሞች ላይ ወጥ በሆነ መልኩ ተፈጻሚ አድርጎታል።

ፊፋ ለሮይተርስ በሰጠው መግለጫ የተጫዋቾችን፣ የዳኞችን፣ የደጋፊዎችንና የሠራተኞችን ጤናና ደህንነት ለመጠበቅ ጽኑ ቁርጠኝነት እንዳለው የገለጸ ሲሆን፣ ውሳኔው በስታዲየም ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችንና ያልተገቡ ድርጊቶችን ለመቀነስ እንደሚያግዝም ታምኖበታል።

በውድድሩ ወቅት በአንዳንድ አዘጋጅ ከተሞች ያለው የሙቀት መጠን 26 እስከ 28 ዲግሪ ሴልሺየስ ሊደርስ እንደሚችል በመገመቱ፣ ደጋፊዎች የመጠጥ ውሃ የሚያገኙበት አማራጭ አሳሳቢ ሆኖ የነበረ ቢሆንም ፊፋ ይህንን ሥጋት ለመቅረፍ ከአዘጋጅ ከተሞችና ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር በመተባበር ሰፊ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።

በዚህም መሠረት በስታዲየሞች ዙሪያ የውሃ ርጭት ጣቢያዎች፣ ግዙፍ ማራገቢያዎች፣ ነጻ የውሃ አቅርቦት ቦታዎች እና የማቀዝቀዣ ድንኳኖች እንዲዘጋጁ የሚደረግ ሲሆን፣ በተጨማሪም በስታዲየም ውስጥ የሚሸጡ የውሃ ጠርሙሶች ዋጋ ከመጠን በላይ እንዳይጨምርና በየስታዲየሞቹ ከዚህ ቀደም ሌሎች ሁነቶች ሲስተናገዱ ከነበረው መደበኛ የዋጋ ተመን ጋር ወጥ እንዲሆን ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ተገልጿል።

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሦስት ሀገራት ማለትም በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ አዘጋጅነት የሚካሄደውና 48 ብሔራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበት የዘንድሮው ዓለም ዋንጫ፣ ከሰኔ 04 እስከ ሐምሌ 12 ቀን 2018 . ይቆያል።

ይህ ታላቅ ውድድር አንድ ተጨማሪ የማጣሪያ ዙር በማካተት የጨዋታ ብዛቱን 64 ወደ 104 ከፍ ስላደረገ በዓይነቱ ልዩ የዓለም ዋንጫ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በላሉ ኢታላ