Search

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሀገራችን የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሕዝቡ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ማሳያ ነው፡- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

ሓሙስ ግንቦት 27, 2018 153

 የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አጠቃላይ ሂደት አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ምርጫው በሀገራችን የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሕዝቡ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ያሳየ ታላቅ ክስተት መሆኑን አስታውቋል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ጎበዜ አበራ በመግለጫቸው እንደጠቆሙት፥ ሕዝቡ በነፃነትና በነቂስ ወጥቶ በሰላማዊ መንገድ የመረጠው ይህ ምርጫ፣ ለሀገራዊ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሕዝቡ ያለውን ፅኑ ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት ነው።

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው በነፃነት መሳተፍ መቻላቸውን ያነሱት ሰብሳቢው፥ የምርጫው አጠቃላይ ሂደት ከጅማሮው አንስቶ እስካሁን ድረስ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መከናወኑን ገልጸዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሳጌ ሻምባ በበኩላቸው፥ በምርጫው ወቅት ሕዝቡ በነፃነት መሳተፍ መቻሉ በሳል የዲሞክራሲ ሥርዓት በመገንባት ረገድ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ በባለቤትነት እንደሚሳተፉ ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በቀሩት የምርጫ ሂደቶች ላይ በተለይም የምርጫ ውጤቱን የማሳወቅ ሂደት በይፋ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በከፍተኛ ትዕግሥት መጠባበቅ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርቧል።

አያይዞም ሁሉም ተፎካካሪ አካላት በዚህ ምርጫ አሸናፊ ከሚሆነው ፓርቲ ጋር በሰላማዊ መንገድ እጅ ለእጅ ተያይዘው ለመሥራት ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ምክር ቤቱ አሳስቧል።

ምክር ቤቱ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነትና ሰላማዊ ፍጻሜ የጎላ አስተዋጽኦ ላበረከቱ መላው አካላት በሙሉ የላቀ ምስጋናውን አቅርቧል።

በትዕግስቱ ቡቼ