Search

የሰላም ተስፋ የፈነጠቀበት አዲስ ምዕራፍ፤ እስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ

ሓሙስ ግንቦት 27, 2018 94

ለረጅም ጊዜ በውጥረት ውስጥ በቆየው የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና አዲስ የሰላም ተስፋ የፈነጠቀ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

እስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነታቸውን ለማደስ እና በደቡባዊ ሊባኖስ የሂዝቦላህ እንቅስቃሴን የሚገድቡ የደህንነት አካባቢዎችን ለመፍጠር መስማማታቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በዋሽንግተን በተካሄደው በአራተኛው ዙር የአሜሪካ አደራዳሪነት ውይይት የተደረሰው ይህ ስምምነት፣ "ሊታኒ" ከተሰኘው ረጅሙ የሊባኖስ ወንዝ እስከ እስራኤል-ሊባኖስ ድንበር ድረስ ያለውን ሰፊ አካባቢ ከሂዝቦላህ ተዋጊዎች ነፃ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ታውቋል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደገለጹት፤ ይህ አዲስ ዕቅድ በሊባኖስ ውስጥ ከሂዝቦላህ ነፃ የሆነ የፀጥታ ቀጣና ለመፍጠር የሚያስችል የተግባር መርሃ ግብርን በውስጡ ያካተተ ነው፡፡

 ሁን እንጂ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የሚሆነው በኢራን የሚደገፈው ሂዝቦላህ ጥቃቶቹን እና ሌሎች ወታደራዊ እንቅስቃሴዎቹን ሙሉ በሙሉ ካቆመ ብቻ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ይህ ተስፋ የፈነጠቀ ድርድር የተደረሰው በደቡባዊ ሊባኖስ በእስራኤል ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ከተገደሉ እና ሂዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል ሮኬቶችን ከተኮሰ በኋላ ሲሆን፣ ይህም በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ተደርሶ የነበረውን ከፊል የተኩስ አቁም ስምምነት ፈተና ውስጥ ጥሎት እንደነበር ይታወሳል፡፡

ስለ አዲሱ ስምምነት ሂዝቦላህ እስካሁን በይፋ የሰጠው አስተያየት ባይኖርም፣ የቡድኑ የፖለቲካ ምክር ቤት አባል ማህሙድ ቃማቲ ቀደም ሲል የተደረሰው ስምምነት የዳሂያ (ደቡብ ቤሩት) ጥበቃ ስምምነት እንጂ ሙሉ የተኩስ አቁም ስምምነት አልነበረም ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

በቀጣይም ሁለቱ ሀገራት ይበልጥ ሁሉን አቀፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ እና ተጨማሪ ውይይቶችን ለማካሄድ በአውሮፖውያኑ አቆጣጠር በሰኔ 22 ቀን እንደገና ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዋል፡፡

በልዩ እሸቱ