Search

ምክር ቤቱ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጸደቀ

ሓሙስ ግንቦት 27, 2018 52

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 23 መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አፅድቋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል የጋራ የባዮሎጂ ምርምር ማዕከል ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አፅድቋል። የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (/) የውሳኔ ሃሳብና ሪፖርት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ በኢትዮጵያና በሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል የጋራ ባዮሎጂካል ምርምር ማዕከል ለማቋቋም የተፈረመው ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል የጋራ ሳይንሳዊ እና ጥናታዊ የምርምር ሥራዎችን ለማጠናከርና ለማሳደግ እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር መሠረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም የምርምር ውጤትን ወደ ገበያ የማቅረብ ተቋማዊ ቅርጽ በማስያዝ የሁለቱ ሀገራት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ምክትል ሰብሳቢው አያይዘው ገልጸዋል፡፡

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን የዓሳ ሀብት ልማት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው እንደመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ለማድረግ ሩሲያ በዘርፉ ካላት ከፍተኛ ልምድ ለማካበት እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል፡፡

በመሆኑም በኢ.... መንግሥት እና በሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል የጋራ የባዮሎጂ ምርምር ማዕከል ለማቋቋም የተፈረመው ስምምነት ረቂቅ አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1421/2018 ሆኖ በሙሉ ድምፅ ጸድቋል።

በተመሳሳይ በኢ.... መንግሥት እና በቬትናም ሶሻሊስት ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የዲፕሎማቲክ ወይም ኦፊሴላዊ የአገልግሎት ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት የተፈረመ ስምምነት ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አፅድቋል።

 የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (/) የውሳኔ ሃሳብና ሪፖርት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

ምክትል ሰብሳቢው በኢ.... መንግሥት እና በቬትናም ሶሻሊስት ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የዲፕሎማቲክ ወይም ኦፊሴላዊ የአገልግሎት ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት የተፈረመው ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል እያደገ የመጣውን የሁለትዮሽ ትብብርንና የዲፕሎማሲ ግንኙነት መስመርን ለማጠናከር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።

እንዲሁም ቪዛ ለማግኘት የሚያስፈልጉትን ቅድመ-ሁኔታዎችና የሚወስደውን ጊዜ በማስቀረት የዲፕሎማቲክ ወይም ኦፊሴላዊ እና አገልግሎት ፓስፖርት የያዙ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ዲፕሎማቶች እንዲሁም ዜጎች በየጊዜው የሚያደርጉት እንቅስቃሴና ጉዞ በቀላሉ እንዲመቻች የሚያደርግ መሆኑን አያይዘው ተናግረዋል።

በመሆኑም በኢ.... መንግሥት እና በቬትናም ሶሻሊስት ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የዲፕሎማቲክ ወይም ኦፊሴላዊ የአገልግሎት ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት የተፈረመው ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 1422/2018 ሆኖ በሙሉ ድምፅ መጽደቁን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።