Search

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጠንካራ መሠረት መጣሉን የኦሮሚያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ

ሓሙስ ግንቦት 27, 2018 42

የኦሮሚያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ሂደት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በክልሉ የሚወዳደሩ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያቀፈው ምክር ቤቱ መግለጫውን ያወጣው፣ የፓርቲዎቹ መሪዎችና ተወካዮች በተገኙበት የምርጫውን አጠቃላይ ሂደት ገምግሞ ካጠናቀቀ በኋላ ነው፡፡

ምክር ቤቱ በመግለጫው ምርጫው የሕዝብ ከፍተኛ ተሳትፎ የታየበትና የአስፈጻሚ አካላት ፍትሐዊነት የተረጋገጠበት መሆኑን አስታውቋል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በምርጫው ሂደት የታየው የሕዝቡ የነቃ ተሳትፎ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማስፈጸም አቅም፣ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ ተስፋ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ በመግለጫው በተለይ ለምርጫው ሰላማዊነት የፀጥታ አካላት የተጫወቱትን ሚና ያደነቀ ሲሆን፣ ምርጫ ቦርድም ሂደቱን ከማስፈጸም ባለፈ የሚነሱ ቅሬታዎችን ከስር ከስር በመፍታት በኩል የነበረውን ጥረት አጉልቷል፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ ኅብረተሰቡ ምርጫውን ለማደናቀፍ የተሰማሩ ኃይሎችን በማምከን፣ ሥልጣን ማግኘት የሚቻለው በምርጫ ካርድ ብቻ መሆኑን በተግባር ያሳየበት ሂደት እንደነበር በአፅንኦት ገልጿል፡፡

ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻ እና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት ያደረጉትን ከፍተኛ ርብርብ ያደነቀው ምክር ቤቱ፣ ሂደቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ስልጡንነት እና መብቱን ለመጠቀም ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ያመላከተ መሆኑን አስታውቋል፡፡ 

በዘሃራ መሀመድ