Search

የድምፅ ግርማ፡ ምርጫው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያፀናበት የታሪክ ምዕራፍ

ሓሙስ ግንቦት 27, 2018 49

ምርጫ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ውስጥ የዜጎችን የፖለቲካ ውክልና ከማረጋገጥ ባሻገር፣ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ጂኦ-ፖለቲካዊ ስትራቴጂካዊ ሀገር ውስጥ የብሔራዊ ህልውና፣ የልዑላዊነት እና የሀገረ-መንግስት ፅናት ማረጋገጫ ቁልፍ ምዕራፍ ነው።

የኢትዮጵያ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የስልጣን ሽግግር ውድድር ብቻ ሳይሆን፣ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት፣ የውስጥ አንድነት እና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞቿን የምታስጠብቅበት የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው።

ምርጫው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አንፃር ያለው ፋይዳ፦

ብሔራዊ ጥቅም የአንድን ሀገር የግዛት አንድነት፣ የኢኮኖሚ ነፃነት እና የፖለቲካ ሉዓላዊነትን ያጠቃልላል። ጠንካራ እና በህዝብ አመኔታ (Legitimacy) ላይ የተመሰረተ መንግስት መፍጠር የብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቂያው ዋነኛ መሳሪያ ነው።

ምርጫው በስኬት መጠናቀቁ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ያላትን የመደራደር አቅም በእጅጉ ያጎለብተዋል። መንግስት ከህዝብ በሚያገኘው የድምፅ ውክልና አማካኝነት እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የባህር በር እና ቀጠናዊ ትስስርን የመሳሰሉ ግዙፍ ሀገራዊ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ፕሮጀክቶችን ያለምንም የውጭ ተፅዕኖ እና መሸማቀቅ ለማስፈፀም የሚያስችል ህጋዊ እና ሞራላዊ አቅም ያጎናፅፈዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን (FDI) ለመሳብ እና ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን ለማስቀጠል የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር መፈጠሩን ለዓለም የሚያረጋግጥበት ትልቁ ማሳያ ነው።

ምርጫው እንዳይሳካ ከሚፈልጉ ኃይሎች ሴራ አንፃር ሲመዘን፦

የምርጫውን ስኬት ብሔራዊ ድል የሚያደርገው ሀገሪቱን ለማዳከም ከሚሰሩ የውስጥ እና የውጭ ኃይሎች ፍላጎት አንፃር ሲተነተን ነው 

 ምርጫው በስኬት እንዳይጠናቀቅ የሚሹ ኃይሎች ዋነኛ ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ የህገ-መንግስት ቀውስ (Constitutional Crisis) መፍጠር እና የስልጣን ክፍተት እንዲፈጠር ማድረግ ነበር።

 እነዚህ ኃይሎች ምርጫው ቢስተጓጎል፣ ቢዘገይ ወይም በሁከት ቢጠናቀቅ፣ ኢትዮጵያ ወደ ሽግግር መንግስት አዙሪት እንድትገባ እና ማዕከላዊው መንግስት ደካማ እንዲሆን ይመኛሉ።

 ደካማ ማዕከላዊ መንግስት ደግሞ የውጭ ኃይሎች በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ በቀላሉ ጣልቃ እንዲገቡ፣ ኢትዮጵያ በቀጠናው ያላትን የጂኦ-ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት እንድታጣ እና ብሔራዊ ጥቅሞቿን አሳልፋ እንድትሰጥ የሚያስገድድ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል።

በመሆኑም ምርጫውን ማክሸፍ ማለት የኢትዮጵያን ሀገረ-መንግስት (Statehood) መሰረት መንቀጥቀጥ እና የብሔራዊ ጥቅሟን አጥር ማፍረስ ማለት እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ።

የህዝቡ ፅናት፣ እልህ እና አኩሪ ተሳትፎ ይህንን ውስብስብ የውስጥ እና የውጭ ሴራ በውል የተረዳው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ምርጫውን የህልውና ጉዳይ አድርጎ ነው የተቀበለው።

 ህዝቡ በምርጫ ዕለት ያሳየው ተነሳሽነት መደበኛ የዜግነት ግዴታን ከመወጣት የዘለለ፣ ሀገርን የማዳን እና የማፅናት ጥልቅ ስሜት የታከለበት ነበር።

በጨለማ፣ በለሊት፣ ብርድ እና ውሽንፍር ሳይበግራቸው፤ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ አዛውንቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና ወጣቶች በነቂስ ወጥተው በረጅም ሰልፍ ድምፃቸውን መስጠታቸው የህዝቡን "እልህ" እና የማይበገር ፅናት ያሳያል።

 ይህ በእልህ የመነጨው "ሀገሬን በካርዴ እጠብቃለሁ፤ የጠላቶቿን ሴራ በድምፄ አከሽፋለሁ" ከሚል የጠለቀ የሀገር ፍቅር ስሜት ነው።

የህዝቡ በንቃት መሳተፍ፣ ምርጫውን ለማደናቀፍ የተጠነሰሱ ሴራዎችን ሁሉ ከንቱ ከማድረጉም በላይ፣ ዜጎች ለሀገራቸው ሉዓላዊነት እና ሰላም ያላቸውን ቀናዒነት በተግባር ያረጋገጠበት ታሪካዊ ክስተት ነው።

ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ሳይቀር የተገረሙበት ይህ የህዝብ ተሳትፎ፣ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ማንም ጣልቃ እንዲገባ እንደማይፈቅዱ ያስመሰከረ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ድል ነው። ምርጫው ሀገርን በማፅናት ያለው ፋይዳ ይህ ታሪካዊ ምርጫ ሀገርን በማፅናት (State Consolidation) ረገድ ያለው ትርጉም እጅግ የላቀ ነው።

አንደኛ፣ የህግ የበላይነትን እና ተቋማዊ አቅምን (Institutional Resilience) በተግባር አሳይቷል። በፈተናዎች መሃል ሆኖ ህዝብን ያሳተፈ ሰላማዊ ምርጫ ማካሄድ መቻል፣ የኢትዮጵያ ተቋማት ጠንካራ መሰረት እየያዙ መምጣታቸውን ያረጋግጣል። 

ሁለተኛ፣ ብሔራዊ መግባባትን ያጠናክራል። ዜጎች በነቂስ ወጥተው የፈለጉትን መምረጣቸው፣ በመንግስት እና በህዝብ መካከል ያለውን ማህበራዊ ውል (Social Contract) ያድሳል፤ ያፀናልም።

በአጠቃለይ፣ ይህ ምርጫ ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት ነው። ህዝቡ በድምፁ ሀገሩን ከሴራ ታድጓል፤ ብሔራዊ ጥቅሟን በፅኑ መሰረት ላይ አቁሟል።

ምርጫው የኢትዮጵያ የውስጥ አንድነት እና የህዝቧ ፅናት ከማንኛውም የውጭ ጫና እና የውስጥ ፈተና በላይ መሆኑን ለዓለም ያወጀበት፣ ኢትዮጵያ በልጆቿ ንቁ ተሳትፎ እና የማይበገር የሀገር ፍቅር ስሜት ከፍ ብላ የታየችበት አንፀባራቂ የድል ምዕራፍ ነው።

በአዶኒያስ /አረጋይ