Search

የኡሁሩ እና የዶ/ር ስፔሲዮዛ እውነት

ሓሙስ ግንቦት 27, 2018 37

 “7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አፈፃፀምን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት በራሳቸው ሊኮሩ ይገባል ሲሉ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የተናገሩት ቃል፣ ከተለመደው የዲፕሎማሲ ማባበያ የዘለለ ጥልቅ ሀገራዊና አህጉራዊ ትርጉም ያዘለ ነው።

ከእሳቸው ጋር በመሆን የኢጋድን የታዛቢዎች ቡድን የመሩት / ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌም፣ የምርጫውን አካታችነት፣ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ይህ የአፍሪካውያኑ ታላላቅ መሪዎች ምስክርነት ከጀርባው አያሌ የፖለቲካ እና የስነ-ልቦና ትርክቶችን የሰበረ ጉልበት አለው።

የኡሁሩ እና የዶ/ ስፔሲዮዛ እውነት፡ ምስክርነትን ያስገደደው የህዝብ ማዕበል፦

እነዚህ አፍሪካውያን መሪዎች ይህንን እውነት ለመግለፅ የተገደዱት ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት በመነጨ ሳይሆን፣ መሬት ላይ የነበረው ተጨባጭ የህዝብ ፅናት (Objective reality) የትኛውንም ታዛቢ የሚያስደምም ስለነበር ነው። 

 / ስፔሲዮዛ እንዳሉት፣ ከዚህ ቀደም በርካታ የአፍሪካ ምርጫዎችን ታዝበዋል፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ ያዩት የተለየ ነበር። 

በጨለማ፣ በብርድ እና በለሊት ወጥቶ ድምፁን ለመስጠት የተሰለፈው ህዝብ፤ ወረፋ ጠብቀው የዜግነት ግዴታቸውን የተወጡት እናቶች፣ ነፍሰ ጡሮች እና አካል ጉዳተኞች ለየትኛውም ዓለም አቀፍ ታዛቢ ልብን የሚነካ እውነት ነው። ታዛቢዎቹ ያዩት ወረቀት ወደ ኮሮጆ ሲገባ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ታላቅ ህዝብ ሀገሩን በድምፁ ሲያክም፣ ሉዓላዊነቱን በካርዱ ሲያፀና እና ለዴሞክራሲ ያለውን የጠማ ቁርጠኝነት በተግባር ሲያሳይ ነው።

 እውነቱ አፍጦ ሲወጣ፣ መመስከር የታሪክ ግዴታ ይሆናል።

የተሰበረው የቆየ ትርክት፡ "አፍሪካውያን በራሳቸው አይችሉም"

ለዘመናት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ በተለይም በምዕራባውያን ዘንድ ተቀርፆ የቆየ አንድ የተሳሳተ ትርክት አለ። 

 አፍሪካውያን በራሳቸው አቅም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ አይችሉም የሚል የስነ-ልቦና ጫና (Paternalistic narrative) በአህጉሪቱ ላይ ሲንፀባረቅ ቆይቷል። ምርጫ በአፍሪካ ሁልጊዜም ከትርምስ፣ ከግጭት እና ከውድቀት ጋር ተያይዞ እንዲሳል ይደረግ ነበር።

የኢትዮጵያው 7 ጠቅላላ ምርጫ ግን ይህንን አሮጌ ትርክት ከመሰረቱ የናደ ነው። ኢትዮጵያውያን የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልጋቸው፣ በራሳቸው የፀጥታ ተቋማት፣ በራሳቸው የምርጫ ቦርድ አስተባባሪነት እና በራሳቸው ህዝብ የነቃ ተሳትፎ እጅግ ሰላማዊ ምርጫ ማካሄድ እንደሚችሉ በተግባር አሳይተዋል። 

ኡሁሩ ኬንያታ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ሊኮሩ ይገባል ያሉትም ይሄንን የአቅም ግንባታ (Self-reliance) እና ተቋማዊ ብስለት በሚገባ ስለተረዱ ነው። ይህ የኢትዮጵያ ስኬት ለአፍሪካውያን ትልቅ የተስፋ ብርሃን እና የራስ መተማመን ምንጭ ነው። 

ያለ ምዕራባውያን ታዛቢዎች የማይፀድቀው የምርጫ "ስሌት" ሲከሽፍ

ሌላው በዚሁ ምርጫ ክፉኛ የተመታው ትርክት፣ "የአፍሪካ ምርጫ ተቀባይነት (Legitimacy) የሚያገኘው በምዕራባውያን ታዛቢዎች የይሁንታ ማህተም ሲረጋገጥ ብቻ ነው" የሚለው ያልተፃፈ ህግ ነው።

 ለዓመታት ምዕራባውያን ተቋማት የአፍሪካን ምርጫዎች እንደራሳቸው የፖለቲካ ፍላጎት ሲያፀድቁ እና ሲያወግዙ ኖረዋል። 

በኢትዮጵያ ምርጫ ግን የታየው እውነት ሌላ ነው። ምርጫው በዋናነት የታዘበው በአፍሪካውያን ወንድሞች (እንደ ኢጋድ እና የአፍሪካ ህብረት ባሉ ተቋማት) ነው። ይህ የሚያሳየው አፍሪካውያን የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው ሚዛን መመዘን ወደሚችሉበት የብስለት ደረጃ መድረሳቸውን ነው።

 የምዕራባውያን ታዛቢዎች አለመኖር የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት፣ የህዝቡን ተሳትፎም ሆነ የሂደቱን ተአማኒነት ቅንጣት ታህል አልቀነሰውም።

ይልቁንም፣ አፍሪካ የራሷን የዴሞክራሲ ተቋማት ማጠናከር እንዳለባት እና ከምዕራባውያን የጥገኝነት አስተሳሰብ መላቀቅ እንዳለባት በግልፅ ያሳየ የአስተሳሰብ አብዮት ነው።

ለታዛቢ ያልተደረገው፣ ለትውልድ የተተከለው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ፦

ከሁሉ በላይ ጎልቶ የሚወጣው ዓለም አቀፋዊ እውነት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫውን ያካሄደው ዓለም አይቶ እንዲያደንቅለት፣ ወይም የውጭ ኃይሎች እውቅና እንዲሰጡት ፈልጎ አለመሆኑ ነው።

 ኢትዮጵያ ምርጫውን ያካሄደችው ዴሞክራሲን ለማፅናት ያላት ፅኑ እና ውስጣዊ ፍላጎት (Endogenous democratic drive) ስላስገደዳት ነው።

ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ዕቃ ሳይሆን፣ የሀገርን ህልውና የማስቀጠል፣ የህዝቦችን አብሮነት የማጠናከር እና ውስጣዊ ሰላምን የማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ነው።

 ህዝቡ በዚያን ያህል እልህ እና ፅናት ሌሊቱን በብርድ አሳልፎ ድምፁን የሰጠው፣ "ዓለም ምን ይለኛል?" ብሎ ሳይሆን፣ "ለልጆቼ እና ለነገዋ ሀገሬ ምን መሰረት እጥላለሁ?" ከሚል ጥልቅ የዜግነት ስሜት በመነጨ ነው። ዓለም ቢታዘበውም ባይታዘበውም፣ ኢትዮጵያዊያን ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የከፈሉት ዋጋ እና ያሳዩት ቁርጠኝነት በማንም ሊቀለበስ የማይችል ሀገራዊ ሐቅ ነው።

በአጠቃላይ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካ ድል ነው። የኡሁሩ እና የዶ/ ስፔሲዮዛ ምስክርነት፣ ኢትዮጵያ የነደፈችው የነፃነት እና የሉዓላዊነት መንገድ ትክክል መሆኑን በታሪክ መዝገብ ላይ ያሰፈረ ነው።

 ህዝቡ ባሳየው አስደናቂ ተሳትፎ፣ "አፍሪካውያን አይችሉም" የሚለውን ትርክት ቀብሮ፣ "ያለ ምዕራባውያን እውቅና አንፀድቅም" የሚለውን ጥገኝነት ሰብሮ፣ በራሱ አንቀሳቃሽ ሞተር (Self-driven) የዴሞክራሲ ጉዞውን በተግባር አረጋግጧል። ኢትዮጵያ አሸንፋለች፤ አፍሪካም በኢትዮጵያ ማሸነፍ ውስጥ የራሷን ብሩህ ተስፋ ተመልክታለች።

በአዶኒያስ /አረጋይ