የጋምቤላ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ነፃ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መካሄዱን አስታወቀ።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ኮማንደር ጋትቤል ቦል በሰጡት መግለጫ እንዳብራሩት፤ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ ያለምንም ተፅዕኖ በነፃነት ድምፁን ለሚፈልገው ፓርቲ የሰጠበት ሰላማዊ፣ አሳታፊና ፍትሐዊ ሂደት ነበር።
ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ እስከ ድኅረ ምርጫ የነበሩት አጠቃላይ ሂደቶች ግልጽነት የሰፈነባቸውና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን የጠቀሱት ሰብሳቢው፤ በክልሉ በሁሉም የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች ሕዝቡ በንቃት መሳተፉንና የምርጫ ሕግን የሚጥስም ሆነ የአሠራር ክፍተት ጨርሶ እንዳልተስተዋለ ገልጸዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ መምህር ሻምበል ቶላ በበኩላቸው፤ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ያለማንም ጣልቃገብነትና ተጽዕኖ በምርጫው መሳተፉን በመግለጽ ሂደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን አብራርተዋል።
የምክር ቤቱ ጸሐፊ አቶ ፔን ኡጁሉ በበኩላቸው፥ ሕዝቡ የዲሞክራሲ መብቱን በመጠቀም ያሳየው ተሳትፎ እጅግ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ምርጫው በሕዝብ ድምፅ አገረ መንግሥትን ለማጽናት ጠንካራ መሠረት የተጣለበት፣ ነፃ፣ ፍትሐዊና ተቀባይነት ያለው መሆኑን አስገንዝበዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝቡ በድምፁ የሰጠውን ውሳኔ በአክብሮት በመቀበል፣ የምርጫው ውጤት በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በኩል ይፋ ሲደረግ በጸጋ መጠበቅና መቀበል እንደሚገባቸው የጋራ ምክር ቤቱ አሳስቧል።
አያይዞም በምርጫው ሂደት የጸጥታ አካላት ፍጹም ገለልተኛ በመሆን የሕዝቡን ደህንነት የማስጠበቅ አገራዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት በመወጣታቸው ምክር ቤቱ የላቀ ምስጋናውን አቅርቧል።
በሚፍታህ አብዱልቃድር