የቡሩንዲው ፕሬዚዳንት ኤቫሪስት ንድዪሺሚዬ የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱን ሊቀመንበርነት ኃላፊነት በይፋ ተረክበዋል።
ፕሬዚዳንቱ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ለጉባኤው ስኬት ላደረገችው ድንቅ ዝግጅት ምስጋና አቅርበው፤ አዲስ አበባ የፓን አፍሪካኒዝም ጽኑ መሠረትና የኅብረቱ መገኛ መሆኗን ዳግመኛ ማስመስከሯን ገልጸዋል።
ለአፍሪካ አንድነትና ነጻነት መሠረት ለጣሉ መስራች አባቶች የላቀ አክብሮት የሰጡት ፕሬዚዳንቱ፤ ቡሩንዲ ይህን ታላቅ አህጉራዊ አደራ በመቀበሏ የተሰማቸውን ኩራት ገልጸዋል።
ኃላፊነቱ ከባድ ቢሆንም በፈጣሪ እርዳታ አህጉሪቱን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ሀገራቸው ቡሩንዲ ያለፈችባቸውን ፈተናዎች በውይይትና በንግግር አልፋ ዛሬ ለመሪነት መብቃቷ ለሌሎች አፍሪካውያን ትልቅ ተስፋ መሆኑን ተናግረዋል።
ቡሩንዲ ለአህጉሪቱ ስኬት ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽንና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርባ እንደምትሠራም ቃል ገብተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም፣ ብዝኃነትን መጠበቅና ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር የቀጣይ የሥራ ዘመናቸው ዋነኛ ትኩረት እንደሚሆንም አመልክተዋል።
የአፍሪካ ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረክ ጎልቶ እንዲሰማና አጀንዳ 2063 ስኬታማ እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
በተጨማሪም የውኃ ደኅንነትን ማረጋገጥና በገጠር ለሚኖሩ ማኅበረሰቦች ንጹህ ውኃ ተደራሽ ማድረግ ሌላው የትኩረት አቅጣጫቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።
ፕሬዚዳንቱ "የአፍሪካ ዕድገትና ልዕልና ዋና መዳረሻችን ነው" በማለት ለአህጉራዊ አንድነት ያላቸውን ጽኑ አቋም በማረጋገጥ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።
በለሚ ታደሰ