Search

አፍሪካ ለሰላም የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ መቀጠል አለባት - የፍልስጤም ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሙስጠፋ

ቅዳሜ የካቲት 07, 2018 87

የፍልስጤም ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሐመድ ሙስጠፋ በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ አፍሪካ ለሰላም የምታደርገው ድጋፍ አጠናክራ መቀጠል አለባት ብለዋል፡፡
አህጉሪቱ ለፍልስጤም ሕዝቦች ነፃነትና ሉዓላዊነት ለምታሳየው የቆየ አጋርነትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል።
በፍልስጤምና በአፍሪካ መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት የሕዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በማክበር ላይ የታነፀ መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይም በልማት፣ በልምድ ልውውጥና በኢኮኖሚ ውህደት ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፤ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የተከሰተው ቀውስ በሕዝቦች ላይ እያደረሰ ያለው ሰብአዊ ጫና አሳሳቢ መሆኑን ለጉባኤው አብራርተዋል።
ግጭቱ በአስቸኳይ ቆሞ ሰላም እንዲሰፍን እንዲሁም ለተጎጂዎች የሚቀርቡ የሰብአዊ ድጋፎች ያለምንም መስተጓጎል የሚደርሱበት ሁኔታ እንዲመቻች ጥሪ አቅርበዋል።
ፍልስጤም በተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች ውስጥ ሙሉ አባልነት ማግኘቷን እንደ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህ ስኬት የአፍሪካ ኅብረት ላደረገው ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በመጨረሻም አፍሪካ በዓለም መድረክ ያላትን ሚና እንድታጠናክር ድጋፋቸውን በመግለጽ፣ ለአህጉሪቱ ሕዝቦች ሰላምና ብልጽግናን ተመኝተዋል።
በመሀመድ ፊጣሞ