Search

የጂኦ-ፖለቲካዊ ቀውሶች፣ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖውና በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድረው አንድምታ

ረቡዕ መጋቢት 09, 2018 188

የሥርዓታዊ ትስስር (Systemic Interconnectivity) ተጋላጭነት

21ኛው ክፍለ ዘመን የዳበረው እጅግ የተሳሰረ የዓለም አቀፍ አቅርቦት ሰንሰለት (Global Supply Chain) አንድ ጂኦግራፊያዊ ጥግ ላይ የሚከሰት የጸጥታ መደፍረስ በሌላኛው የዓለም ጫፍ ላይ ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ንዝረት (Economic Shock) እንዲፈጥር አድርጓል። በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን  መካከል በመካከለኛው ምሥራቅ የተከፈተው ወታደራዊ አውድማ፣ ከቀጠናዊ የፖለቲካ ፍጥጫ አልፎ የዓለምን ኢኮኖሚያዊ ደም ስር ወደ ማነቅና ንዝረት ወደ መፍጠር ተሸጋግሯል።

 

1.የሆርሙዝ ሰርጥ እና ስትራቴጂካዊ የባህር ላይ "የጉሮሮ ነጥቦች" (Global Choke Points)

የዓለም አቀፍ ጂኦ-ፖለቲካ ትንታኔዎች እንደሚጠቁሙት፣ የዓለም የንግድ ደህንነት የተመሰረተው በጥቂት ጠባብ የባህር ላይ መተላለፊያዎች (Choke points) ላይ ነው። ከነዚህም መካከል የሆርሙዝ ሰርጥ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።

 የኢነርጂ ጂኦ-ፖለቲካ (Energy Geopolitics) የሆርሙዝ ሰርጥ በቀን በአማካይ 20 እስከ 21 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ (የዓለምን 20 በመቶ ፍጆታ) የሚያስተላልፍ ስትራቴጂካዊ መስመር ነው። ኢራን ይህንን መስመር በከፊልም ሆነ በሙሉ ለመዝጋት የምታደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ፣ ዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦትን እንደ ፖለቲካዊ የጦር መሣሪያ (Weaponization of Energy Supply) የመጠቀም ስትራቴጂዋ አካል ነው።

• ከሆርሙዝ እስከ ባብ-ኤል-ማንደብ፦ ቀውሱ በሆርሙዝ ብቻ የተገደበ አይደለም። በየመን የሚገኙት የሁቲ አማጽያን በቀይ ባህር መግቢያ በሆነው ባብ-ኤል-ማንደብ ሰርጥ ላይ የሚያደርሱት ጥቃት፣ የእስያ-አውሮፓን የንግድ መስመር ክፉኛ አስተጓጉሎታል። እነዚህ ሁለት ስትራቴጂካዊ የጉሮሮ ነጥቦች በአንድ ጊዜ ስጋት ውስጥ መውደቃቸው የዓለምን ሎጂስቲክስ የታነቀና ሽባ እያደረገው ይገኛል።

 

2.ዓለም አቀፍ ማክሮ-ኢኮኖሚያዊ መናወጥ፡ "ስታግፍሌሽን" (Stagflation) ስጋት

የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ የዓለምን ኢኮኖሚ ወደ አደገኛ አዙሪት እየከተተው መሆኑን ዐበይት የኢኮኖሚ ማመላከቻዎች ያሳያሉ፦

የአቅርቦት ሰንሰለት መቋረጥ እና የሎጂስቲክስ ወጪ ንረት (Supply Chain Disruption) መርከቦች ከቀይ ባህር መስመር በመሸሽ ረጅሙን የደቡብ አፍሪካ 'ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ' (Cape of Good Hope) መስመር ለመጠቀም መገደዳቸው፣ የጉዞ ጊዜውን አሁን ባለው አንፃራዊ መረጃ 10 እስከ 15 ቀናት አራዝሞታል። ይህ ሁኔታ የዓለም አቀፍ የጭነት ትራንስፖርት ክፍያን (Freight indices) 300% በላይ አሻቅቦታል።

የነዳጅ ዋጋ መዋዥቅ እና ገቢራዊ የዋጋ ግሽበት (Imported Inflation) የነዳጅ ዋጋ በአንድ በርሜል 100 ዶላር ጣሪያን መንካቱ ወይም በከፍተኛ ሁኔታ መዋዠቁ፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በትራንስፖርት ዘርፎች ላይ የግብዓት ወጪን ይጨምራል። ይህ ወጪ በቀጥታ ወደ ሸማቹ ስለሚተላለፍ፣ የዓለምን ማዕከላዊ ባንኮች (እንደ US Federal Reserve ያሉት) የወለድ ምጣኔን (Interest Rates) ረዘም ላለ ጊዜ ከፍ አድርገው እንዲያቆዩ ያስገድዳቸዋል።

የስታግፍሌሽን አደጋ፦ ታዋቂው የማክሮ-ኢኮኖሚ ምሁር ኑሪየል ሩቢኒ (Nouriel Roubini) እንደሚያስጠነቅቁት፣ እንዲህ ያለው የጂኦ-ፖለቲካዊ የኃይል ቀውስ ዓለምን ወደ ስታግፍሌሽን (Stagflation)—ማለትም የኢኮኖሚ ዕድገት መቀዝቀዝ (Stagnation) እና ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት (Inflation) በአንድ ላይ ወደሚከሰትበት ክፉ አዘቅትይከታታል ሲሉ ይደመጣሉ።

 

3.የአፍሪካ ቀንድ የጂኦ-ስትራቴጂካዊ ተጋላጭነት

የአፍሪካ ቀንድ ከቀይ ባህር እና ከኤደን ባህረ ሰላጤ ጋር ባለው ጂኦግራፊያዊ ቁርኝት ምክንያት፣ የዚህ ዓለም አቀፍ ግጭት ቀጥተኛ ማዕበል ማረፊያ (Shock Absorber) ሆኗል።

የቀይ ባህር ወታደራዊነት (Militarization of the Red Sea) የንግድ መስመሩን ለመጠበቅ በሚል ሰበብ በርካታ የዓለም ኃያላን ሀገራት የጦር መርከቦቻቸውን በቀይ ባህር አሰማርተዋል። ይህ ሁኔታ ቀጠናውን ወደ ዓለም አቀፍ የውክልና ጦርነት (Proxy War) አውድማነት እየቀየረው ሲሆን፣ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን ሉዓላዊነትና የፖለቲካ መረጋጋት በእጅጉ ይፈታተናል።

የወደብ ኢኮኖሚ መዳከም፦ በዚሁ ግጭት ሰበብ አለም አቀፍ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የጅቡቲ፣ የፖርት ሱዳን እና የበርበራ ወደቦች እንቅስቃሴ በቀይ ባህር ላይ በተጋረጠው ስጋት ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል። ይህም በቀጥታ የወደብ አገልግሎትን እንደ ዋና የገቢ ምንጭ ለሚጠቀሙ ሀገራት የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ እያስከተለ ነው።

 

4.የግጭቱ ቀጥተኛ አንድምታ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ሥነ-ምኅዳር ምን ማለት ነው?

ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛትም ሆነ እያደገ በመጣው ፈጣን የኢኮኖሚ አቅሟ የአፍሪካ ቀንድ ግዙፍ ኢኮኖሚ ብትሆንም  በታሪካዊና ፖለቲካ ስህተት ምክንያት ከውሃ እንድትርቅ ተደርጎ በመቆየቷ (የባህር በር አልባ መሆኗ)  ለከፍተኛ የወደብ ኪራይ እና ሌሎች ተደማሪ ከሎጂስቲክስ ጋር የተያያዙ ወጪዎችና ጫናዎችን ተሸክማ ያለች ሀገር ናት፡፡ ይህ አለም አቀፋዊ ተፅእኖ በኢትዮጵያ ላይ ጫናዎችን ማሳረፉ የማይቀር ነው፡፡

ኢትዮጵያ እንደሌሎች ሀገራት ሁሉ  ነዳጅ አስመጪ ሀገር ናት። ያውም ነዳጅን ለህዝቧ ደህንነትና ኢኮኖሚያዊ ጫናን ለመቋቃም ሲባል ከፍተኛ ድጎማ በማድረግ የአለም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በህዝቡ ላይ በቀጥታ እንዳያርፍ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ አሁንም ቢሆን የዓለም የነዳጅ ዋጋ መናር መንግሥት በነዳጅ ላይ የሚያደርገውን የድጎማ በጀት እንዲያሻቅብ ያደርገዋል፤ ይህም የመንግሥትን ለተለያዩ የልማት ስራዎች ሊያውለው የነበረውን በጀት ይሻማል ማለት ነው።

የሎጂስቲክስና የመርከብ ትራንስፖርት ወጪ መጨመርና አቅጣጫ ለውጥ የገቢ ዕቃዎች እና የኤክስፖርት ምርቶች ጫና ማሳደሩ ማይቀር ጉዳይ ነው፡፡

ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ስጋት ሲጨምር፣ ባለሀብቶች ካፒታላቸውን ስጋት-አልባ ወደሆኑ (Safe Havens) እንደ አሜሪካ ቦንድ ወይም ወርቅ ወደመሳሰሉት የማሸሽና የግል ዘርፉ (Privatization) እና ኢንቨስትመንት ላይ ጫና ሊያሳድር ይችላል፡፡

 

የኢትዮጵያ መንገድ

የኢኮኖሚ ማዕበል መቋቋም የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ የፖሊሲ ሽግግሮችና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት

 

1.የኃይል ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እና የነዳጅ ጥገኝነትን መስበር

የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ የነዳጅ ዋጋን ወደ ሰማይ ሲሰቅለው፣ ኢትዮጵያ ቀድማ የወሰደቻቸው የኃይል ፖሊሲ ለውጦች ሀገሪቱን ከከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ክስረት ታድገዋታል።

• የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች (EV) አብዮት፦ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ባወጡት የጋራ ፖሊሲ፣ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ የቀረጥ ማበረታቻ በማድረግ ይህ ፖሊሲ ሀገሪቱ በየዓመቱ ለነዳጅ ግዥ ከምታወጣው 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ላይ ጉልህ ቅናሽ እንዲመጣ እያደረገ ነው።

• የታላቁ ሕዳሴ ግድብ እና የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት፦ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅና ኃይል ማመንጨት መጀመር፣ እንዲሁም በፀሐይ እና በንፋስ ኃይል የተደረጉ ኢንቨስትመንቶች፣ ኢትዮጵያ የሀይል ፍላጎቷን በሀገር ውስጥ ታዳሽ ኃይል እየተካች የአረንጓዴ ኢኮኖሚ አውራ እየሆነች መሄዷን ያሳያል፡፡

 

2. የምግብ ሉዓላዊነት እና የገቢ ምርት መተካት (Import Substitution)

ዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ሲቋረጥ (በተለይ ከሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትና ከቀይ ባህር ቀውስ ጋር ተያይዞ) የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ሆኗል።

• የበጋ ስንዴ ልማት ስትራቴጂ፦ መንግሥት "ስንዴን ከውጭ ማስገባት ማቆም አለብን" በሚል የጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ ኢትዮጵያን ከስንዴ አስመጪነት ወደ ራስን መቻል፣ አልፎም ወደ ውጭ ገበያ መላክ (Export) አሸጋግሯታል። የዓለም ባንክ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ ይህ እርምጃ ሀገሪቱ ለስንዴ ግዥ ታወጣ የነበረውን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር አድኖላታል።

• የግብርናው ዘርፍ ዘመናዊነት፦ የኩታ ገጠም እርሻ መስፋፋት እና የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን በሀገር ውስጥ ለማምረት የተጀመሩት ጥረቶች፣ ከዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ መስተጓጎል የሚመጣውን ጫና ቀንሰውታል።

 

3.ማክሮ-ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች (HGER II)

የገንዘብ ሚኒስቴር ተግባራዊ ያደረገው ሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ (Homegrown Economic Reform - Phase II) መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ ነው።

• የፋይናንስ ዘርፍ ሊበራላይዜሽን፦ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መፍቀዱ እና የቴሌኮም ዘርፉን ክፍት ማድረግ (የሳፋሪኮም መግባት) የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን (FDI) ከመሳቡም በላይ የካፒታል እጥረትን ለመቅረፍ ረድቷል።

• የኤክስፖርት ብዝኃነት (Export Diversification) ኢትዮጵያ ከባህላዊው የቡና ኤክስፖርት በተጨማሪ በማዕድን (በተለይ ወርቅ) በማኑፋክቸሪንግ እና በአገልግሎት ዘርፎች ላይ ያደረገችው ማሻሻያ ገቢዋን አሳድጎታል። IMF በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች ቢኖሩም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሰሃራ በታች ካሉ አፍሪካ ሀገራት አማካይ ዕድገት በተሻለ ፍጥነት እያደገ መሆኑን አረጋግጧል።

 

ሲጠቀለል

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የወሰደቻቸው እነዚህ የፖሊሲ እርምጃዎች፣ ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን በውስጣዊ አቅም (Resilience) ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ጥለዋል። "መደመር" የፖለቲካ ፍልስፍና ብቻ ሳይሆን፣ የተበታተነ ሀብትን አስተባብሮ በታዳሽ ኃይል፣ በግብርና እና በዲጂታል ኢኮኖሚ የሀገርን ሉዓላዊነት በተግባር የማረጋገጥ ሒሳብ መሆኑን እነዚህ ስትራቴጂዎች ያረጋግጣሉ። የገንዘብ ሚኒስቴር እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ይህ መንገድ የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ ብልጽግና የሚያረጋግጥ ነው።

ፈተናዎች አይግጠሙ አይባልም፣ ነገር ግን ፈተናዎችን ወደ እድል የመቀየር አቅም የዚህ ዘመንና ትውልድ የኢትዮጵያ መገለጫና አቅም መሆኑ በተግባር ታይቷል፡፡ ይህ ሁኔታ በሰሜኑ ጦርነት  ፣ይህ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት በተግባር ታይቷል፡፡ አሁንም አለም በተለያዩ ጦርነቶች እና ፈተናዎች ስትታመስ  የኢትዮጵያ መንገድ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ያደሩ ችግሮቻችንን ጭምር በማቃለል ነገን ብሩህ የሚያደርግ አማራጭ መሆኑ በተጨባጭ ተረጋግጧል፡፡

መልካም ቀን!!

በአዶንያስ ወልደአረጋይ