Search

የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ላስከተለው የነዳጅ እጥረት የሀገራት ስትራቴጂያዊ ምላሽ

ሓሙስ መጋቢት 10, 2018 83

በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ግጭት ሦስተኛ ሳምንቱን በያዘበት በአሁኑ ወቅት፣ በዓለም የነዳጅ ንግድ የደም ዝውውር ተብሎ በሚጠራው የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የጦርነት ደመና አጥልሏል።

በአየር እና በባህር ኃይል ጥቃት የታጀበው ይህ ውጥረት፣ የዓለምን የነዳጅ ገበያ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እያናረው ይገኛል።

የሆርሙዝ ወሽመጥ አለመረጋጋት ለዓለም ኢኮኖሚ ትልቅ ስጋት መሆኑን የተረዱ ሀገራት፣ የሚጠበቀውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመቋቋም የተለያዩ ስልታዊ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምረዋል።

ዋሽንግተን የነዳጅ ገበያውን ለማረጋጋት ስትራቴጂካዊ የነዳጅ ክምችቷን (Strategic Petroleum Reserve) ወደ ገበያ በማስገባት ላይ ትገኛለች።

ሆኖም ይህ እርምጃ የሀገሪቱን መጠባበቂያ ክምችት በታሪክ ዝቅተኛው ደረጃ ላይ እንዲያርፍ በማድረጉ፣ ለወደፊቱ ብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ሊሆን እንደሚችል ተንታኞች ያስጠነቅቃሉ።

ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ ሳዑዲ ዓረቢያን ጨምሮ የኦፔክ አባል ሀገራት የምርት መጠናቸውን እንዲጨምሩ ብርቱ የዲፕሎማሲ ግፊት እያደረገች ነው።

የዓለማችን ግዙፏ ነዳጅ አስመጪ ቻይና፣ የባሕር ላይ ጥገኝነቷን ለመቀነስ በሩሲያ እና በመካከለኛው እስያ በኩል የሚመጡ የየብስ የነዳጅ ቧንቧዎችን እንደ ዋነኛ አማራጭ እየተጠቀመችባቸው ነው።

ቤጂንግ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አጠቃቀም በማፋጠን፣ ከነዳጅ ጥገኝነት ለመውጣት የረጅም ጊዜ ስትራቴጂዋን በተግባር እያዋለችው ትገኛለች።

እንደ ጀርመን እና ፈረንሳይ ያሉ የአውሮፓ ሀገራት የኑሮ ውድነቱ በዜጎቻቸው ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ የኤክሳይዝ ታክስ ቅነሳን እንደ ጋሻ ተጠቅመዋል።

በኃይል አቅራቢ ኩባንያዎች ላይ የዋጋ ተመን በመጣልም የችርቻሮ ዋጋው እንዳያሻቅብ ብርቱ ቁጥጥር እያደረጉ ነው።

በሌላ በኩል 80 በመቶ በላይ የነዳጅ ፍላጎቷን በገቢ ምርት የምታሟላው ህንድ፣ ፊቷን ወደ ላቲን አሜሪካ እና አፍሪካ በማዞር አዳዲስ የነዳጅ ምንጮችን በማሰስ ላይ ናት።

የሆርሙዝ ወሽመጥ ውጥረት ሀገራት በነዳጅ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ዳግም እንዲፈትሹ እያደረጋቸው ነው። ይህ ጂኦ-ፖለቲካዊ ግፊት ዓለም ወደ ታዳሽ የኃይል ምንጮች የምታደርገውን ሽግግር ይበልጥ እንደሚያፋጥነው ይገመታል።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ

#EBC #WorldNews #EnergyCrisis #OilMarket