Search

በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተው ጦርነት በታሪክ ከፍተኛውን የኢነርጂ እጥረት አስከትሏል - የዓለም ኢነርጂ ባለሥልጣን

ቅዳሜ መጋቢት 12, 2018 53

ሦስተኛ ሳምንቱን የያዘው እና በዓለም ሀገራት ላይ ከባድ ቀውሶችን ይዞ የመጣው የአሜሪካ-እስራኤል እና የኢራን ጦርነት በተለይ በኢነርጂ ዘርፉ ላይ ትልቅ ጫናን አሳድሯል።

የዓለም አቀፉ የኢነርጂ ባለሥልጣን ሥራ አስፈጻሚ ፋቲህ ቢሮል የተፈጠረውን ችግር ሲያብራሩ፣ በጦርነቱ ምክንያት የተዘጋው የሆርሙዝ ሰርጥ በኢነርጂው ዘርፍ ላይ በታሪክ ውስጥ ትልቁን ስጋት እና እጥረት አስከትሏል ብለዋል።

የሆርሙዝ ሰርጥ በቀን ወደ 20 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የሚተላለፍበት 20 በመቶ የዓለማችን የተፈጥሮ ጋዝ ንግድ የሚከናወንበት ወሳኝ ቀጣና ነው።

ይህ መስመር በቶሎ ወደ ሥራ ካልገባ በዓለማችን ሀገራት ላይ የታየው ተጽዕኖ ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

በዓለም ላይ ዋና ዋና የነዳጅ አምራች ከሚባሉት ካናዳ፣ ሜክሲኮ፣ ብራዚል ጋር ተጨማሪ አቅርቦቶች ጋር ውይይቶች ቢካሄዱም የመካከለኛው ምሥራቅ የኃይልን ምርት ማካካስ እንደማይችሉ አስታውቀዋል።

እንደ መፍትሔ ካነሷቸው ሐሳቦች መካከል የአውሮፓ ሀገራት በሩሲያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ሙሉ በሙሉ በማንሣት የተፈጠረውን ጫና ማቃለል እና ተጨማሪ የመጠባበቂያ ነዳጅ ወደ ገበያው ማሰራጨት የሚሉት ተጠቅሷል።

በዋናነት ግን የዓለም ሀገራት ከነዳጅ ኃይል በመላቀቅ ወደ ታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት የሚያደርጉትን ሽግግር እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በብዛት መጠቀም የኑክሌር ኃይልን መጠቀም እና የንፋስ እና የፀሐይ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም የነዳጅ ኃይል ላይ ያለውን ጥገኝነት መቀነስ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በሀብተሚካኤል ክፍሉ

#EBC #Ethiopia #Energy #MiddleEast