የሆርሙዝ ወሽመጥ በዓለም ላይ እጅግ ወሳኙ የነዳጅ ማስተላለፊያ እና መተላለፊያ ተደርጎ ይወሰዳል። በ2024 በየቀኑ በአማካይ 20 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ በዚህ ጠባብ የውኃ መስመር ውስጥ ያልፋል፤ ይህም በዓለም ላይ በየቀኑ ጥቅም ላይ ከሚውለው ጠቅላላ የነዳጅ መጠን ውስጥ አንድ አምስተኛው (1/5ኛው) ማለት ነው። በዚህ መስመር ላይ የሚፈጠር ማንኛውም መስተጓጎል በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ፣ በምርት አቅርቦት ሰንሰለት እና በሀገራት ኢኮኖሚ ላይ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከፍተኛ መናወጥ አስከትሏል።
መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጡ እና የቦታው ጠባብነት
ወሽመጡ የፋርስ ባህረ ሰላጤን ከኦማን ባህረ ሰላጤ እና ከህንድ ውቅያኖስ ጋር ያገናኛል። በሰሜን በኩል ኢራንን፣ በደቡብ በኩል ደግሞ የኦማንን ሙሳንዳም ልሳነ-ምድር ይለያል። ወሽመጡ በጣም ጠባብ በሚሆንበት ቦታ 35 ማይልስ (56 ኪሎ ሜትር) ብቻ ስፋት ቢኖረውም፣ ግዙፍ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ሊጓዙበት የሚችሉት መስመር ግን በጣም የተገደበ ነው። መርከቦች የሚገቡበትና የሚወጡበት መስመሮች እያንዳንዳቸው 2 ማይልስ (3 ኪሎ ሜትር) ብቻ ስፋት ሲኖራቸው፣ በመካከላቸውም የ2 ማይልስ (3 ኪሎ ሜትር) መከፋፈያ ቦታ አለ።

ይህ ማለት የዓለም የባህር ላይ ነዳጅ ንግድ በአጠቃላይ 6 ማይልስ (9 ኪሎ ሜትር) ብቻ ስፋት ባለው ጠባብ ኮሪደር ውስጥ ያልፋል ማለት ነው። ከፋርስ ባህረ ሰላጤ ለመውጣት ሌላ አማራጭ የባህር መንገድ የለም። ሳውዲ አረቢያ፣ ኢራቅ፣ ኩዌት፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኳታር ነዳጅና ተፈጥሮአዊ ጋዝ ለዓለም ለመላክ በዚህ ብቸኛ መተላለፊያ ላይ ጥገኞች ናቸው።
በመስመሩ የሚያልፈው የኃይል መጠን
በአውሮፓውያኑ 2024 በዚህ ወሽመጥ የሚያልፈው ነዳጅ በዓለም ላይ በባህር ከሚጓጓዘው ጠቅላላ የነዳጅ ንግድ ውስጥ ከአንድ አራተኛ (1/4ኛ) በላይ ይሸፍናል። ይህም ድፍድፍ ነዳጅን፣ ቤንዚንና ናፍጣ እንዲሁም ሌሎች የነዳጅ ውጤቶችን ያካትታል። ከነዳጅ በተጨማሪ የዓለም 20% የፈሳሽ ተፈጥሮአዊ ጋዝ ንግድ በዚህ መስመር ያልፋል። በተለይ ኳታር እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለእስያና አውሮፓ ሀገራት ለኤሌክትሪክ ማመንጫና ለቤት ማሞቂያ የሚውል ጋዝ የሚያቀርቡት በዚህ መስመር ነው።
የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተፅዕኖው
የሆርሙዝ ወሽመጥ ነዳጅ ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች እንደ ቻይና፣ ሕንድ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ያሉ የለእስያ ሀገራት ናቸው። ለእነዚህ ሀገራት በመስመሩ ላይ የሚፈጠር መስተጓጎል የፋብሪካዎቻቸውን ሥራ፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴንና የኤሌክትሪክ ኃይል መረጋጋትን በቀጥታ አደጋ ላይ ይጥላል።
ይሁን እንጂ ነዳጅን ቀጥታ ከዚህ መስመር የማያስገቡ ሀገራት እንኳ ተፅዕኖው ያርፍባቸዋል። የነዳጅ ዋጋ የሚወሰነው በዓለም አቀፍ ገበያ በመሆኑ፣ 20 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ከገበያ ቢጠፋ ወይም መጥፋቱ ቢሰጋ ዋጋው በሁሉም ቦታ ይንራል፤ ይህም የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል።
ኢራን እና ዓለም አቀፍ ሕጋዊ ውዝግቦች
ኢራን በወሽመጡ ሰሜናዊ ክፍል ረጅም የባህር ጠረፍ ስላላት ከፍተኛ መልክዓ-ምድራዊ ብልጫ አላት። ቴህራን በተለያዩ ጊዜያት ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦች ወይም ወታደራዊ ስጋቶች ሲደቀኑባት መተላለፊያውን የመዝጋት ማስፈራሪያ ስታሰማ መቆየቷ የሚታወቅ ነው። በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እንደ ሆርሙዝ ያሉ ወሽመጦች ወታደራዊ መርከቦችን ጨምሮ ለማንኛውም መርከብ ክፍት መሆን ቢገባቸውም፣ ኢራን ግን ወታደራዊ መርከቦች አስቀድመው ፈቃድ እንዲጠይቁ ትፈልጋለች፤ ይህም በየጊዜው ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ውጥረት ሲፈጥር ቆይቷል። አሁን ደግሞ የወሽመጡ መዘጋትን ተከትሎ የዓለም ንግድ አደጋ ውስጥ ወድቋል።

ሌሎች አማራጮች አሉ?
ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ወሽመጡን ሳይጠቀሙ ነዳጅ በየብስ ለማጓጓዝ የሚያስችሉ የቧንቧ መስመሮችን ቢገነቡም፣ እነዚህ መስመሮች አሁን በወሽመጡ የሚያልፈውን ከፍተኛ የነዳጅ መጠን ሙሉ በሙሉ ሊተኩ አይችሉም። ለተፈጥሮአዊ ጋዝ ደግሞ ምንም ዓይነት አማራጭ የቧንቧ መስመር የለም፤ ኳታር ሙሉ በሙሉ በወሽመጡ ላይ ጥገኛ ናት።
የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ማለት የነዳጅ ዋጋ ከ100 ዶላር በላይ እንዲጨምር ሊያደርግ እንደሚችል ቀድሞ የተገመተ ቢሆንም አሁን በተግባር ይሄው ሆኗል። የትራንስፖርት ወጪ እንዲጨምር እና የዓለም ኢኮኖሚ ለከፋ ቀውስ እንዲጋለጥ የሚያደርግ በመሆኑ ቦታው ለዓለም ሰላምና መረጋጋት እጅግ ወሳኝ ነው።
በጌቱ ላቀው