Search

ለፕሬዚዳንት ትራምፕ የተኩስ አቁም ጥሪ የኢራን ምላሽ ምንድን ነው?

ማክሰኞ መጋቢት 15, 2018 72

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ሊሰነዘር የነበረው ጥቃት ለ5 ቀናት እንዲቆም ማዘዛቸውንና ከኢራን ጋር "ውጤታማ ንግግር" መጀመሩን ቢገልጹም፣ ቴህራን ግን የቀረበውን የድርድር ጥሪ ውድቅ ማድረጓ ተሰምቷል።
የኢራን የበላይ መሪ ምክር ቤት ወታደራዊ አማካሪ ሞህሰን ረዛኢ በሰጡት መግለጫ፣ በጦርነቱ ለደረሰው ውድመት ሙሉ ካሳ እስካልተከፈለና በኢራን ላይ የተጣሉት የኢኮኖሚ ማዕቀቦች ሙሉ በሙሉ እስካልተነሱ ድረስ ጦርነቱ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
አማካሪው አክለውም "አሜሪካ በዚህ ጦርነት የድል መንገድ እንደሌለ ተረድታለች" ያሉ ሲሆን፣ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን አሜሪካን ለተጨማሪ ጦርነት እየገፋፉ ነው ሲሉ ከሰዋል።
የኢራን ፓርላማ አፈ-ጉባኤ መሀመድ ባገር ቃሊባፍ በበኩላቸው፣ ከአሜሪካ ጋር ምንም ዓይነት ድርድር አለመደረጉንና የተሰራጨው መረጃ የነዳጅ ገበያን ለመቆጣጠር የታለመ "የሀሰት ዜና" ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋኢም ቢሆኑ፣ ስቲቭ ዊትኮፍ እና ያሬድ ኩሽነር ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተዋል የሚለውን የትራምፕ ንግግር አስተባብለዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ዕለት በትሩዝ ማህበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ካልከፈተች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎቿን እንደሚያወድሙ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ ግን ለ5 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም አውጀዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የትራምፕን ውሳኔ እንደሚደግፉ ገልጸው፣ እስራኤል ግን በኢራንና በሊባኖሱ ሂዝቦላህ ላይ የምታደርገውን ጥቃት እንደምትቀጥል አስታውቀዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የገቡበት ወታደራዊ ግጭት 24ኛ ቀኑ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ኢራን ጦርነቱን ለማቆም የኢስላማዊ ሪፐብሊኩ መብት እንዲከበር፣ የካሳ ክፍያ እንዲፈጸም እና ዳግም ጥቃት እንዳይሰነዘር ዓለም አቀፍ ዋስትና እንዲሰጥ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጣለች።
በጌቱ ላቀው