በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣው ግጭትና ኢራን የዓለም የነዳጅ የልብ ትርታ የሆነውን የሆርሙዝ የባሕር ሰርጥን መዝጋቷ፣ ዓለምን ለኃይል ቀውስ ዳርጎታል።
በአሜሪካና በእስራኤል የተሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ ኢራን በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ፣ በሰርጡ ለማለፍ በሚሞክሩ መርከቦች ላይ ጥቃት እየተፈጸመ በመሆኑ የዓለም የነዳጅና የጋዝ ፍሰት ተገትቷል።
ይህ ድንገተኛ ክስተት ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን ለማንቀሳቀስና ውስን የሆነውን የነዳጅ ክምችታቸውን ለመቆጠብ እጅግ አስገዳጅና ያልተለመዱ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፉ አስገድዷቸዋል።
በእስያ ሀገራት ዘንድ ቀውሱ እጅግ በርትቶ የሚታይ ሲሆን፣ ስሪላንካ ለዜጎቿ የነዳጅ ኮታ በመቁረጥ በሳምንት 15 ሊትር ብቻ እንዲፈቀድ በQR-ኮድ አሠራር ወስናለች።
ባንግላዲሽና ፓኪስታን የሥራ ቀናትን በመቀነስና ትምህርት ቤቶችን ወደ ኦንላይን በማዞር ኃይልን ለመቆጠብ እየጣሩ ይገኛሉ።
በአፍሪካም ግብፅ የንግድ ማዕከላትና የመንግሥት ሕንፃዎች ከምሽቱ 3 ሰዓት ጀምሮ እንዲዘጉ መመሪያ ስታወጣ፣ ኬንያ ደግሞ ያላት ክምችት እስከ ሚያዝያ ወር ብቻ የሚበቃ በመሆኑ የነዳጅ ምርቶችን ወደ ውጭ መላክ አግዳለች።
ኒውዚላንድም ቢሆን በረራዎችን በመሰረዝ "መኪና የማይነዳበት ቀን" የተባለውን ጥንታዊ ፖሊሲ ዳግም ለመተግበር እያሰበች ትገኛለች።
ምንም እንኳ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቴህራን ጋር "ውጤታማ ንግግር" መጀመሩንና ጥቃቶች ለአምስት ቀናት እንዲራዘሙ መደረጉን ቢገልጹም፣ ኢራን ግን መረጃውን አስተባብላለች።
ይህ ዓለም አቀፍ ቀውስ የነዳጅ ዋጋን ከማናሩ ባለፈ፣ ሀገራት ወደ ፊት የኃይል ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ አዳዲስ ስልቶችን እንዲከተሉ ትልቅ ማስጠንቀቂያ ሆኗል።
የሆርሙዝ ሰርጥ ዝግ ሆኖ መቆየት ማለት የዓለም ኢኮኖሚ መታፈን በመሆኑ፣ መላው ዓለም በትልቅ ስጋትና በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውስጥ ይገኛል።
መሀመድ ፊጣሞ