26ኛ ቀኑን የያዘውና ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እያስከተለ የሚገኘው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ተባብሶ በቀጠለበት በዚህ ወቅት፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግጭቱን ለማስቆም ያስችላል ያሉትን ባለ 15 ነጥብ የሰላም ዕቅድ ይፋ አድርገዋል።
ይህ ዕቅድ በኢራን እና በምዕራባውያን መካከል ያለውን የቆየ ቅራኔ በመፍታት በቀጣናው ዘላቂ መረጋጋትን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
በፕሬዚዳንት ትራምፕ የቀረበው የሰላም ስምምነት ሰነድ ኢራን ያበለጸገችውን ዩራኒየም እንድታስረክብ፣ ለዓለም ዓቀፉ የአቶሚክ ኃይል ተቆጣጣሪ (IAEA) በሯን ክፍት እንድታደርግ፣ በባለስቲክ ሚሳኤልና በድሮን ምርቷ ላይ ገደብ እንድታበጅ ይጠይቃል።
በተጨማሪም ቴህራን ለሂዝቦላህ፣ ለሀማስ እና ለሌሎች የታጠቁ አካላት የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም እንዲሁም የሆርሙዝ ሰርጥን ለትራንስፖርት ክፍት ማድረግ እንደሚጠበቅባት በዕቅዱ ተካትቷል።
ኢራን እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች የምታከብር ከሆነ አሜሪካ በበኩሏ በሀገሪቱ ላይ የጣለቻቸውን የኢኮኖሚና የነዳጅ ማዕቀቦች እንደምታነሳና ኢራን ወደ ዓለም አቀፉ የባንክ ሥርዓት እንድትመለስ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ ስምምነቱ ያብራራል።
ይህ የሰላም ጥሪ የቀረበው ግንባር ላይ ያለው ውጥረት በከረረበት ወቅት ሲሆን፣ ኢራን በአሜሪካ የጦር ሰፈሮችና በእስራኤል ላይ፣ በምላሹ ደግሞ አሜሪካና እስራኤል በቴህራንና በተለያዩ የኢራን ከተሞች ላይ ጥቃት እያደረሱ መሆኑን አናዶሉና ኒውዮርክ ታይምስ ዘግበዋል።
የኢራን ባለሥልጣናት እስከአሁን በዕቅዱ ላይ ምላሽ ባይሰጡም፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሂደቱን በንቃት እየተከታተለ ይገኛል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ
#Geopolitics #TrumpPeacePlan #MiddleEastCrisis #NuclearDeal #HormuzStrait