Search

የነዳጅ ዘመን እያበቃ ይሆን? በ2030 የታዳሽ ኃይል አጠቃቀም በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምር ነው

ሓሙስ መጋቢት 17, 2018 143

ዓለማችን በትራንስፖርት ዘርፍ የምትጠቀመው የታዳሽ ኃይል መጠን እስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ በ50 በመቶ ያህል እንደሚያድግ አዲስ የወጣ መረጃ አመላክቷል።
ይህ ታላቅ ለውጥ በተለይም በታዳሽ ኤሌክትሪክ፣ በባዮ ነዳጅ (Biofuels) እና በሃይድሮጅን የኃይል ምንጮች ላይ የሚታይ ይሆናል።
የዚህ ታሪካዊ ዕድገት ትልቁን ድርሻ (45 በመቶ) የሚይዘው ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚውል የታዳሽ ኤሌክትሪክ ኃይል ሲሆን፣ በተለይም በቻይና እና በአውሮፓ የሚታየው የተሽከርካሪዎች ሽግግር ለውጡን በግንባር ቀደምትነት ይመራዋል።
እንደ ብራዚል፣ ሕንድ እና ኢንዶኔዥያ ባሉ ሀገራት ደግሞ ከዕፅዋት የሚቀመም የባዮ ነዳጅ አጠቃቀም ለዕድገቱ ሁለተኛውን ትልቅ ድርሻ እንደሚይዝ ተገልጿል።
በጥናቱ ትንበያ መሠረት እስከ 2030 ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 15 በመቶ ያህሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ይሆናሉ።
በተለይ በቻይና የተሽከርካሪዎች ዋጋ እየቀነሰ እና የኃይል መሙያ መሠረተ ልማቶች እየተስፋፉ በመምጣታቸው፣ በሀገሪቱ መንገዶች ላይ ከሚታዩ ሦስት መኪኖች አንዱ የኤሌክትሪክ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በአቪዬሽን እና በባሕር ትራንስፖርት ዘርፍም አዳዲስ ሕጎች መውጣታቸውን ተከትሎ የታዳሽ ነዳጅ አጠቃቀም የ10 በመቶ ዕድገት እንደሚያሳይ ተጠቁሟል።
ምንም እንኳን አንዳንድ የሃይድሮጅን ነዳጅ ፕሮጀክቶች በኢንቨስትመንት ውሳኔ መዘግየት ምክንያት ዝቅተኛ ግምት ቢሰጣቸውም፣ አጠቃላይ የትራንስፖርት ዘርፉ ወደ አረንጓዴው ጉዞ የሚያደርገው ግስጋሴ ግን በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚቀጥል ተረጋግጧል።
ይህ ለውጥ የአየር ብክለትን በመቀነስ እና ለወደፊቱ ንጹህ ከተሞችን ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ተስፋን የሰነቀ ነው።
በቢታንያ ሲሳይ