በአሜሪካ ውስጥ በሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ላይ የወደቀ የሜትሮይት አለት ከፕላኔቷ ምድር የበለጠ ዕድሜ እንዳለው የዘርፉ ተመራማሪዎች ገለፁ።
የጆርጂያ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች አለቱን ሲያጠኑ አለቱ ከ4.56 ቢሊዮን ዓመታት በፊት፤ ወይም ምድር ከመፈጠሯ ከ 20 ሚሊዮን ዓመታት በፊት መፈጠሩን ደርሰንበታል ብለዋል።
የጠፈር አለቱ በሰማይ ላይ ሲበር የታየ ሲሆን በመጨረሻም በአየር ላይ ሳለ ፈንድቶ ቁርጥራጩ በሄንሪ ካውንቲ በሚገኘው ማክዶኖፍ ከተማ ውስጥ ያለን 1 ቤት ጣሪያ በስቶ መግባቱን ናሳ አስታውቋል።
በጆርጂያ እና በአቅራቢያዋ ባሉ ግዛቶች ያሉ ሰዎች እሳት የሚመስል የኳስ ቅርጽ ያለው ቁስ ማየታቸውን እና ከፍተኛ ድምጽ መስማታቸውን እንደተናገሩ ቢቢሲ ዘግቧል።
ከቤቱ ውስጥ የተገኙት የሜትሮይት አለት ቁርጥራጮች ለሳይንስ ተመራማሪዎች የተሰጡ ሲሆን እነሱም አለቱ "ቾንዳይት" በመባል የሚታወቅ የሜትሮይት ዓይነት መሆኑን ደርሰውበታል።
የማክዶኖው ሜትሮይት የሚል ስያሜ የተሰጠው አለት በጆርጂያ የተገኘ 27ኛው የጠፈር አለት ነው ።
ጂኦሎጂስት የሆኑት ስኮት ሃሪስ እንዳሉት እንደዚህ አይነት ክስተቶች በጥቂት አስርት ዓመታት አንድ ጊዜ ብቻ ይከሰቱ የነበር ቢሆንም፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ እየታዩ መሆኑን ገልፀዋል።
ሳይንቲስቶች ወደፊት ትላልቅ የጠፈር ድንጋዮች ሚያሳድሩትን አደጋዎች በመረዳት፤ ይህንን ሜትሮይት ማጥናት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
በሴራን ታደሰ