የታሪክ ምጸትና የጂኦ-ፖለቲካዊ ተቃርኖ
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በታላቅ የታሪክ ምጸት የተሞላ ነው። በዓለም ላይ ጥንታዊ እና ገናና ከሚባሉ የባሕር ላይ ሥልጣኔዎች አንዱ ባለቤት የሆነችው፤ የቀይ ባሕርን የንግድ እና የጦር እንቅስቃሴ በበላይነት ትቆጣጠር የነበረችው፤ የጥንታዊቷ የአክሱም ሥልጣኔ ወራሽ ሀገር፤ ዛሬ በዓለም ላይ ወደብ ከሌላቸው (Landlocked) ሀገራት መካከል በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ ሆና ትገኛለች።
ይህ ሁኔታ ተፈጥሯዊ ግዴታ ሳይሆን፣ የታሪክ ስህተቶች፣ የፖለቲካ ሻጥሮች እና የተቀነባበሩ የጂኦ-ፖለቲካዊ ሴራዎች ድምር ውጤት ነው። ጥያቄው፦ "ኢትዮጵያ ከባሕር ኃይል አውራነት ወደ የየብስ እስረኝነት የተሸጋገረችው በምን ዓይነት መዋቅራዊ ስህተት ነው?" የሚለው ይሆናል።
የታሪክ አሻራ፦ ከአዱሊስ እስከ ባሕር ኃይል ሞገስ
ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት የቀይ ባሕር ባለቤት ነበረች። ጥንታዊው የአዱሊስ ወደብ የአክሱም ግዛት የኢኮኖሚ ደም ሥር እና የዓለም የንግድ መስመር ማዕከል ነበር። በ19ኛው ክፍለ ዘመን የቅኝ ገዥዎች የቀይ ባሕርን ዳርቻ መቆራረስ ከመጀመራቸው በፊት፣ አካባቢው በኢትዮጵያ ሉዓላዊ አስተዳደር ሥር የነበረ መሆኑን ታሪካዊ መዛግብት ያረጋግጣሉ።
በዘመናዊው የታሪክ ምዕራፍ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በታኅሣሥ 2 ቀን 1950 (እ.አ.አ) የጸደቀው የውሳኔ ሐሳብ ቁጥር 390(A) ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል ሲወስን፣ ለውሳኔው ዋነኛ ምክንያት የሆነው ኢትዮጵያ ያላት ታሪካዊ እና ሕጋዊ የባሕር በር የመጠቀም መብት ነው። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር ቀጠና ብቁ እና የተከበረ ኃይል ሆኖ ለዓመታት ዘልቋል። "ዓባይ ፪" እና "ራስ ደጀን" የተሰኙት ግዙፍ መርከቦቻችን የቀይ ባሕርን ማዕበል እየቀዘፉ የሉዓላዊነታችን ምስክሮች ነበሩ።
የሴራ ማነቆ፦ የየብስ እስረኝነት እንደ ፖለቲካ ስልት
ኢትዮጵያ ወደብ አልባ እንድትሆን የተደረገው በታሪክ አጋጣሚ ሳይሆን፣ ሀገራችን በቀጠናው ያላትን የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ተጽዕኖ ለመገደብ በተቀነባበሩ የውጭ እና የውስጥ ሴራዎች ነው።
- የቅኝ ግዛት ውሎች፦ ጣሊያን በግንቦት 2 ቀን 1889 (እ.አ.አ) የተፈረመውን የውጫሌ ስምምነትን በክህደት በመጣስ እና ጥር 1 ቀን 1890 (እ.አ.አ) ኤርትራን የራሷ ቅኝ ግዛት አድርጋ በማወጇ፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር በቅኝ ገዥዎች ቁጥጥር ሥር እንዲውል የመጀመሪያው መሠረት ተጣለ።
- የውስጥ ድክመቶች፦ የ1983ቱ (ዓ.ም) የሥልጣን ሽግግር ወቅት፣ የአሰብ ወደብን ጉዳይ ከፖለቲካ ውሳኔው ነጥሎ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሥር እንዲቆይ ለማድረግ የሚያስችል ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ባለመደረጉ፣ ሀገሪቱ በአንድ ጀምበር የባሕር ጠረፏን አጣች። ይህ "የታሪክ ሻጥር" ዛሬ ለሚከፈለው በቢሊዮን የሚቆጠር የወደብ ኪራይ እና ለኢኮኖሚ ማነቆው ዋናው ምክንያት ነው።
ወሳኙ የኢኮኖሚ ማነቆ - የባሕር በር ማጣት ዋጋ
የባሕር በር ማጣት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት በቃላት ከሚገለጸው በላይ ነው።
1. የሎጂስቲክስ እና የትራንዚት ወጪ፦ ኢትዮጵያ የወጪ እና ገቢ ንግዷን ለማካሄድ በጅቡቲ ወደብ ላይ 95% ጥገኛ ናት። ለዚህም በየዓመቱ እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ ለወደብ ኪራይ ትከፍላለች።
2. የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት መዳከም፦ ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦችም ሆኑ ወደ ውጭ የሚላኩ የኢትዮጵያ ምርቶች (ቡና፣ ሰሊጥ፣ ማዕድን) በከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ ምክንያት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነታቸው ይቀንሣል።
3. ብሔራዊ ደኅንነት (National Security)፦ ነዳጅ፣ ማዳበሪያ እና መድኃኒት የመሳሰሉት ስትራቴጂካዊ ግብዓቶች የሚገቡት በሌላ ሀገር ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ በማለፍ ነው። ይህ አደጋ (Choke point) በቀላሉ የኢትዮጵያን ኅልው እና ስጋት ላይ ሊጥል የሚችል ነው።
ሕግ እና ዓለም አቀፍ እውነታዎች
ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄዋን የምታቀርበው በጉልበት ሳይሆን በሕግ እና በታሪክ መሠረት ነው።
- የባሕር ሕግ (UNCLOS)፦ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ብትሆንም፣ የዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ ስምምነቶች ወደ ባሕር የመውጣት እና የመጠቀም (Right of Access) መብትን ያረጋግጣሉ።
- የቅኝ ግዛት ውሎች ኢ-ሕጋዊነት፦ የቅኝ ግዛት ውሎች የቅኝ ገዥዎችን ፍላጎት ለማሳካት የተቀረጹ እንጂ የአፍሪካውያን ፍላጎት መገለጫ አይደሉም። ጣሊያን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሸንፋ ስትወጣ፣ በ1947ቱ የፓሪስ ስምምነት መሠረት በቅኝ ግዛቶቿ ላይ ያላትን መብት በሙሉ አሳልፋ ሰጥታለች።
የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት - ከልቅሶ ወደ ተግባር
ያለፉት ትውልዶች ስህተት ሠርተው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ስህተቱን ማረም የዚህ ዘመን ትውልድ ኃላፊነት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ጊዜያት እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን እንዴት እንዳጣች የሚያሳይ "ምንም ዓይነት ኦፊሴላዊ ሰነድ ወይም ተቋማዊ ውሳኔ" በዝርዝር የለም። ይህ የሚያሳየው ጉዳዩ በቸልተኝነት እና በሴራ የታለፈ መሆኑን ነው።
ኢትዮጵያ ወደ ባሕር መመለሷ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው። የአሰብ ወደብ እና የቀይ ባሕር ዳርቻዎች ታሪካዊ ባለቤታቸውን ኢትዮጵያን ይጠብቃሉ።
ከሴራ ማነቆ ተላቅቆ ወደ ባሕር አድማስ መሻገር የዛሬው ትውልድ ለነገዋ የበለጸገች ኢትዮጵያ የሚያበረክተው ትልቁ የታሪክ ስጦታ ይሆናል።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
#Ethiopia #SeaAccess #RedSea #NoMoreLandLocked #EBC