Search

መካከለኛው ምሥራቅ በጦርነት እና በዲፕሎማሲ መካከል፤ አዲሱ የሰላም ጭላንጭል እና የነዳጅ መስመሮች ተስፋ

ዓርብ መጋቢት 18, 2018 110

ባለፉት 12 ሰዓታት በመካከለኛው ምሥራቅ የታየው ወታደራዊ ግጭት እና ተስፋ ሰጭ የዲፕሎማሲ ጥረቶች ቀጣናውን በውጥረት እና በተስፋ መካከል አቁመውታል። 

እስራኤል በኢራን ላይ የምታደርገው ድብደባ እና የቴህራን አጸፋ የቀጠለ ቢሆንም፣ ከዋሽንግተን እና ከቤጂንግ የተሰሙ መግለጫዎች ግን በጦርነቱ ደመና ውስጥ የሰላም ብርሃን ፈንጥቀዋል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን እና አሜሪካ መካከል የሚደረገው ድርድር በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ሲገልጹ፣ ኢራን በበኩሏ አሥር የነዳጅ ጫኝ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እንዲያልፉ መፍቀዷ ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሔው በጎ ጅምር ተደርጎ ተወስዷል።

አልጀዚራ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ ሳቢያ ሊከሰት የሚችለውን ዓለም አቀፍ የነዳጅ እጥረት ለመታደግ የቀጣናው ሀገራት አማራጭ የነዳጅ መስመሮችን በስፋት መጠቀም መጀመራቸው ለኢኮኖሚው መረጋጋት ሌላኛው ተስፋ ሆኗል።

በተለይም ሳዑዲ ዓረቢያ በቀን 7 ሚሊዮን በርሜል የማሳለፍ አቅም ያለውን "ኢስት-ዌስት" የነዳጅ ቧንቧ መስመር በከፍተኛ ሁኔታ ሥራ ላይ ያዋለች ሲሆን፣ ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ የነዳጅ ፍሰቱ በቀን 770 ሺህ ወደ 2.9 ሚሊዮን በርሜል ማደጉ ተመልክቷል። 

በተያያዘም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትቶች የፉጃይራህ መስመርን እና ኢራቅ የቱርክን የነዳጅ ማስተላለፊያ በመጠቀም የዓለምን የነዳጅ ፍላጎት ለማሟላት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

እነዚህ አማራጭ መስመሮችም የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት የሚያስከትለውን ጫና በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ረገድ እንደ ትልቅ የኢኮኖሚ መተንፈሻ ታይተዋል።

በሌላ በኩል የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ አሜሪካ እና ኢራን ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን የሚጠቁሙ ምልክቶች በመታየታቸውአዲስ የሰላም ጭላንጭልመፈጠሩን ገልጸዋል።

ድርድሩን በዋናነት እያስተባበረች የምትገኘው ፓኪስታን በቅርብ ቀናት ውስጥ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ፊት ለፊት እንዲወያዩ ጥረት እያደረገች መሆኑም ተመልክቷል።

በፈረንሳይ እየተካሄደ ባለው የሰባቱ ኃያላን ሀገራት (G7) ስብሰባ ላይም የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የቀጣናውን ዘላቂ መረጋጋት አስመልክተው መምከራቸው የዲፕሎማሲው እንቅስቃሴ ዓለም አቀፋዊ ትኩረት ማግኘቱን ያሳያል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በበኩሉ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሁን የታየውን የድርድር ዕድል እንዲጠቀም ጥሪ አቅርቧል።

ቀጣናው ዛሬም በጦርነት እና በሰላም መካከል ባለች ጠባብ መስመር ላይ ቢገኝም፣ የተጀመሩት ዲፕሎማሲያዊ እና የሰላም ጥረቶች ለዘላቂ መረጋጋት ተስፋ ሰጪ ሆነዋል።

በለሚ ታደሰ 

#MiddleEastCrisis #TrumpPeacePlan #DiplomacyNow #StraitOfHormuz #PakistanMediation