በአሜሪካ እስራኤል እና ኢራን ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የሆርሙዝ ወሽመጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለማስቀጠል የሚያስችል አዲስ ግብረ ኃይል እያቋቋመ መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት አስታውቋል::
ይህ ግብረ ኃይል የዲፕሎማሲያዊ እና የቴክኒክ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ገልጸዋል።
ግብረ ኃይሉ በዩክሬን የጥቁር ባሕር የእህል ስምምነት እና በጋዛው የUN2720 የእርዳት አቅርቦት ሥርዓት ተሞክሮዎች ላይ በመመስረት ስራውን እንደሚጀምር ታውቋል።
የተመድ የፕሮጀክት አገልግሎት ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ጆርጅ ሞሬራ ዳ ሲልቫ የሚመሩት ይህ ግብረ ኃይል፣ ከሚመለከታቸው ሀገራት ጋር በመነጋገር የንግድ መርከቦች በሰላም እንዲያልፉ የሚያስችል መመሪያ ያዘጋጃል።
ይህም በተለይ በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠውን የማዳበሪያና የነዳጅ አቅርቦት በማስተካከል፣ በድሃ ሀገራት ላይ እያያንዣበበ ያለውን የምግብ ዋጋ ንረትና ለመቀነስ ትልቅ ተስፋ ሆኗል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም ጦርነቱ እስከ ሰኔ ወር ከቀጠለ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፋ ችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉ ማስጠንቀቁ የሚታወስ ነው::
የመንግስታቱ ድርጅት አዲሱ ጥረት ይህንን ስጋት ለመቀልበስ ያለመ ሲሆን ቃል አቀባዩ ዱጃሪክ እንዳሉት፣ ሁሉም አባል አገራት ለሰብዓዊነት ሲሉ ይህንን ተነሳሽነት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በጌቱ ላቀው