የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋሽንግተንና ቴህራን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ንግግር እያደረጉ መሆኑን በመግለጽ፣ አዲሶቹን የኢራን መሪዎች "ምክንያታዊ ናቸው" ሲሉ መግለጻቸው ለሰላማዊ መፍትሔ አዲስ ተስፋን የፈነጠቀ ይመስላል።
ፕሬዝዳንቱ አሜሪካ በኢራን "የመንግሥት ለውጥ" አምጥታለች ብለው እንደሚያምኑ የጠቀሱ ሲሆን፣ ፓኪስታንም ለአንድ ወር የዘለቀውን ጦርነት ለማቆም የሚያስችል "ትርጉም ያለው ድርድር" ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች ተብሏል።
ይህ የሰላም ጥረት ቢኖርም ግን በሺህዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ቀጣናው በመግባት ላይ መሆናቸውና የኢራን ፓርላማ አፈ-ጉባኤ መሐመድ ባከር ካሊባፍ አሜሪካን "ስለ ድርድር እያወራች ወረራ እያቀደች ነው" በሚል መውቀሳቸው ሁኔታውን ዳግም ወደ ውጥረት የተመለስ መስሏል።
በምድር ላይ ያለው እውነታ ግን አሁንም እጅግ አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል፤ እስራኤል ሰኞ ማለዳ ላይ ከየመን የተተኮሱ ሁለት ድሮኖችን ማክሸፏን አስታውቃለች።
ይህም በኢራንና በአሜሪካ-እስራኤል ጥምረት መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ከየመን የተሰነዘረ ሁለተኛው ጥቃት ሆኖ ተመዝግቧል።
በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የየመን ሁቲ አማጽያን ባለፈው ቅዳሜ ወደ እስራኤል ሚሳኤሎችን በመተኮስ ጦርነቱን መቀላቀላቸው ቀጣናዊ ግጭቱ ላይ ተጨማሪ ችግር ቢሆንም አሁንም የዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እንደቀጠሉ ነው።
ለአንድ ወር የዘለቀው ይህ ጦርነት፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ የኢነርጂ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል በመፍጠር የዓለም ኢኮኖሚን ክፉኛ እየጎዳ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰላማዊ መንገድን በመፈለግ ላይ ነው።
በመሀመድ ፊጣሞ