በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ታሪክ ውስጥ ያለፍንባቸው ስምንቱ መጋቢቶች፣ የሀገራችን የለውጥ ጉዞ እና አዲስ የተስፋ አድማስ የሚያመለክቱ ኅያው ምዕራፎች ናቸው።
መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በርዕሰ መንግሥትነት ቃለመሐላ ከፈጸሙበት ጊዜ አንሥቶ፣ የ“መደመር” እሳቤ ሁለንተናዊ የሀገር ግንባታ ፍኖተ-ካርታ እና የተግባር መመሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ይህም ያለፉ ስኬቶችን በማስቀጠል፣ ስህተቶችን በማረም እና ለነገ አዲስ ተስፋን በመፍጠር ላይ የቆመ ፍልስፍና ነው።
ከ2010 ዓ.ም በፊት የነበረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድባብ ሐሳብን በጠላትነት በሚፈርጅ እና በከፍተኛ የለውጥ ናፍቆት የተሞላ ነበር።
የለውጡ የመጀመሪያ ፍሬ የፖለቲካ ምኅዳሩን በማስፋት የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት እና በስደት የነበሩ ተፎካካሪዎችን ወደ ሀገር ማስገባት ሆነ።
ዛሬ ላይ "ጠላት" የሚለው ቃል እየከሰመ "ተፎካካሪ" የሚለው እየተለመደ የመጣ ሲሆን፣ በጠመንጃ አፈሙዝ ፋንታ በሐሳብ የበላይነት የማመን ጅምሮ ታይቷል።
እንደ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ያሉ ተቋማት መቋቋማቸውም የትውልዶችን ቋጠሮ በውይይት ለመፍታት የተወሰደ ታሪካዊ እርምጃ ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት መጋቢቶች በውጭ ግንኙነት ረገድም የተከተለችው ስልት፣ የሀገራችንን ክብር እና ብሔራዊ ጥቅምን ያስጠበቀ ድል የታየበት ነው።
"ጎረቤቴ ሰላም ካልሆነ እኔ ሰላም አልሆንም" በሚል መርሕ፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የነበረውን የዓመታት ቁርሾ በመፍታት የቀጣናው የሰላም ምሰሶ ሆናለች።
በተለይም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተጋረጡባትን ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች በብልህነት በመመከት፣ የመልማት መብቷን እና ሉዓላዊነቷን ለዓለም አስመስክራለች።
የብሪክስ (BRICS) አባል መሆኗም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከአሮጌው የርእዮተ-ዓለም ወገንተኝነት ተላቅቆ ብሔራዊ ጥቅሟን ተንተርሶ መገንባቱን ያረጋግጣል።

በኢኮኖሚ ረገድም ኢትዮጵያ የተከተለችው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከሸማችነት ወደ አምራችነት አሸጋግሯታል።
ትልቁ ማሳያ ደግሞ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን ወደ ውጭ መላክ መጀመሯ እና በሚሊዮን ኩንታል የሚቆጠር የምርት ዕድገት ማስመዝገቧ ነው።
መንግሥት ብቻውን የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ የነበረበትን አሠራር በመቀየር፣ የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው ሞተር እንዲሆን የሚያስችሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።
በተጨማሪም እንደ አዳማ፣ ሐዋሳ እና ድሬዳዋ ያሉ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የሽግግሩ መሠረት ሆነዋል።

ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የታገዘ ኢኮኖሚ ለመገንባት በጀመረችው ጉዞም፣ ውጤታማነትን እና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ስኬቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች።
የመንግሥት አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል መቀየራቸውም ቢሮክራሲንና ሙስናን በመቀነስ ለዜጎች ምቹ አሠራር ፈጥሯል።
ባለፉት ስምንት መጋቢቶች የሰዎች አኗኗር እና የሥራ ባህልም በመሠረታዊነት ተቀይሯል።
"ክትመት" ከተማን በቆዳ ስፋት ከመለጠጥ አውጥቶ ወደ ማስተሳሰር የሚያሸጋግር ፍልስፍና ሆኖ የመጣ ሲሆን፣ የኮሪደር ልማቱ ለሰው ልጅ ምቹ እና ጽዱ ከተሞችን የመፍጠር ስኬት ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርም ባለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች እንዲተከሉ በማድረግ የደን ሽፋኑን በማሳደግ ረገድ ትውልድ ተሻጋሪ ትሩፋት ሆኗል። እነዚህ ፕሮጀክቶች የሀገራችንን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ የዜጎችን የኑሮ ጥራትና የሥነ-ልቦና ከፍታ አረጋግጠዋል።
በመሆኑም የስምንቱ መጋቢቶች ጉዞ ኢትዮጵያ በገጠሟት ውስብስብ የኅልውና ፈተናዎች ፊት ከመንበርከክ ይልቅ፣ ከመከራዋ ውስጥ አዲስ አቅም ፈጥራ ለላቀ ከፍታ መዘጋጀቷን ያሳያል።
የሰሜኑ ጦርነት፣ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሳቢያ የታዩ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የመሰሉ ተግዳሮቶች በመደመር አስተሳሰብ ወደ ዕድል ተቀይረዋል።
ዛሬ ስምንተኛው መጋቢት ላይ ቆመን ወደ ኋላ ስንመለከት የምናየው የትናንትናውን ስኬት ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ፊት በጠንካራ ሀገራዊ መሠረት ላይ ሆነን የምንራመድበትን ጽኑ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ መደላድል ጭምር ነው።
በበረከት ሽመልስ
#EBC #Ethiopia #Change #Horizonofhope