(የዕለቱ መልእክት)
ግንቦት 24 ቀን የተካሄደው 7ኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ፣ ሀገራችን በፈተናዎች እቶን ውስጥ አልፋ ወርቅ ሆና የወጣችበት እና አዲሱን የዴሞክራሲ ታሪኳን በደማቅ ቀለም የጻፈችበት ታሪካዊ ዕለት ነው።
ኢትዮጵያ የገጠሟትን ውስብስብ የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎች በብልኃት እና በጥበብ በማለፍ፣ ሉዓላዊነቷን እና ተቋማዊ ብስለቷን ለዓለም ኅብረተሰብ በተግባር አሳይታለች።
ይህ ምርጫ የአንድ ወገን ወይም የፖለቲካ ድርጅት ድል ሳይሆን በአንድነትና በጽናት የቆመው የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ድል እና የሀገራችን ዘላቂ አሸናፊነት የተረጋገጠበት ማኅተም ነው።
ይህንን ታሪካዊ እውነት የዐይን እማኝ በመሆን የመሰከሩት የአኅጉራችን እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ታዛቢዎች የሰጡት ዕውቅና የድላችንን ታላቅነት ያጎላዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን መሪ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሰለጠነ፣ የሰከነ እና የጸና የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ሲያደንቁ፣ የኢጋድ ታዛቢ ቡድን መሪ ዶክተር ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ በበኩላቸው፣ በሂደቱ የታየውን አካታችነት፣ የሴቶች እና የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ እንዲሁም ሕዝቡ ያሳየውን የላቀ ባሕላዊ መስተንግዶ እና ሰላማዊ አብሮነት በየትኛውም ሀገር አይተውት እንደማያውቁ በኩራት መስክረዋል።
የአውሮፓ ኅብረት፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ እና ስዊዘርላንድ በጋራ ያወጡት መግለጫም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ገለልተኝነት እና በሀገር በቀል አቅም የበለጸገውን "ምርጫዬ" የተሰኘውን የዲጂታል መራጮች ምዝገባ ቴክኖሎጂ አድንቋል።
ይህ "ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ" የመነጨበት እውነታ፣ ቅኝ ተገዝታ የማታውቀው የነጻነት ምልክቷ ኢትዮጵያ ዛሬም ለአኅጉሪቱ የዴሞክራሲና የሉዓላዊነት አዲስ ተምሳሌት መሆን እንደምትችል ያረጋገጠ ነው።
ምርጫው ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ የላቀ ነው። ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በኃይል ሳይሆን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ በምርጫ ካርድ ለመፍታት የተደረገው ልምምድ የሀገራዊ ብስለታችን ማሳያ ነው።
ማናቸውንም ቅሬታዎች በሰለጠነ መንገድ በሕግ አግባብ ብቻ ለመፍታት የተያዘው ቁርጠኝነት ወደፊት ለሚገነባው ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት የማይናወጥ መሠረት ጥሏል ።
ምርጫው በራሱ ፍጻሜ ሳይሆን ዜጎች በሀገራቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ በቀጥታ የወሰኑበት እና የሕግ የበላይነት የነገሠባትን ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የተራመድነው ታላቅ እርምጃ ነው።
አሁን ከምርጫው ማግስት የሚጠበቀው ትልቁ እና ታሪካዊው አደራ "ከመረጡ በኋላ መተባበር፣ ካረሱ በኋላ መዝራት" ነው። "አንድ ሰው ብቻውን ቢጮህ ድምፅ አይሆንም፣ አንድ እንጨት ብቻውን አይነድም" እንደሚባለው፣ ምርጫው በአሸናፊነት መጠናቀቁ የጋራ ሥራችን መጀመሪያ እንጂ ማጠቃለያ አይደለም።
በምርጫው ሂደት የታዩትን ልዩነቶች በሙሉ ወደ ጠረጴዛ በማምጣት፣ በብሔራዊ መግባባት ላይ የተመሠረተች፣ የዜጎቿን እኩልነት እና ብልጽግና ያረጋገጠች የጸናች ሀገርን በጋራ መገንባት የሁላችንም የቤት ሥራ ነው።
አሸናፊዋን ኢትዮጵያን ይበልጥ ለማጽናት፣ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር እና የጀመረችውን የዴሞክራሲ ጉዞ ዳር ለማድረስ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ በፍቅርና በወንድማማችነት ልንተባበር እና ልንሠራ ይገባል።
ማንም ይመረጥ ማን፣ በውጤቱ ላይ የኢትዮጵያ ታላቅነትና ሕዝባዊ አንድነት ከፍ ብሎ እንዲኖር ማድረግ የነገው ብሩህ ተስፋችን ዋስትና ነው።
ኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል