የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባሕር ቀጣና የኃያላን ሀገራት የጂኦ-ፖለቲካ ፍላጎት ማረፊያ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ ቀጥተኛ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት ከሀገር ሕልውና እና ከኢኮኖሚ ነጻነት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ታሪካዊ ጥያቄ ነው።
ከ130 ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገራችን፣ የወጪና ገቢ ንግዷ በአንድ የወደብ አማራጭ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆኑ የሚያሳድርባትን ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ሥጋት ለመቀነስ የባሕር በር ማግኘት የግድ የሚላት ሰዓት ላይ ነች።
ለአንድ ወደብ የሚከፈለው ከፍተኛ የኪራይ ወጪ የሀገራችንን ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነት የሚያሳጣ ከመሆኑም ባለፈ፤ በቀጣናው የሚከሰቱ ድንገተኛ ፖለቲካዊ መስተጓጎሎች የ130 ሚሊዮን ሕዝብ አቅርቦትን በአንድ ጀንበር አደጋ ላይ የመጣል አቅም ያለው ነው።
በመሆኑም የባሕር በር ባለቤት የመሆን ስልታዊ ግብ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ጂኦ-ፖለቲካዊ ሚዛን ለማስከበር፣ የንግድ ወጪዋን ለመቀነስ እና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ያላትን ቀጥተኛ ትስስር ለማጠናከር ለምታደርገው ጥረት ዋነኛ አካል ሆኖ ተወስዷል።
ይህንን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ደግሞ እርስ በርስ በመሠረተ-ልማት መተሳሰር እና ከቀጣናው ሀገራት ጋር የጋራ ዲፕሎማሲያዊ አቅም መገንባት ወሳኝ ተደርጎ ይወሰዳል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት በጋራ ተጠቃሚነት እና በኢኮኖሚያዊ ውህደት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገራትን ሉዓላዊነት በማክበር ፍላጎቷን በጠረጴዛ ዙሪያ በማቅረብ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የገበያ ዕድል፣ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን እንዲሁም የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን በመጠቀም በጋራ የመልማት አቅምን ማካፈል የምትችል በመሆኑ፣ የጎረቤት ሀገራትም በቀጥታ ተጠቃሚ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ይሆናል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ